ለልጄ ምን ብዬ ልንገራት? (አንዲት የጂግጂጋ ኗሪ እናት)

ለልጄ ምን ብዬ ልንገራት? (አንዲት የጂግጂጋ ኗሪ እናት)

መልስ ባገኝም ባላገኝም የተፈጸመብኝን ግፍ እናገራለሁ፡፡ የእኔ በደል በምን ይካሳል? ቁስሌ በምን ይድናል?

የ4 ዓመት ልጄን እንደታቀፍሁ ለ3 ቀናት በቤተ ክርስቲያን ተጠልየ ቆይቼ ዛሬ ቤቴ ገባሁ፡፡ ቤቴ ተዘርፏል፡፡ በባዶ ፍርስራሽ ቤት ኩርምት ብያለሁ፡፡ ልጄ በርሃብ ተዳክማብኝ ነበርና የሶማሌ እናቶች የሚበላ ነገር አምጥተውልኝ አቀመስኋት፡፡ እህል በአፏ እንደዞረ ተነቃቃች፡፡ የልጅ ነገር… ምንም እንዳልተፈጠረ መጫወት ጀመረች፡፡ ከዘረፋው የተረፉ እቃዎችን በማስተካከል እያገዘችኝ እያለ በመሐል… ጠየቀችኝ፡-

‹‹እማዬ… ባለፈው እኮ ፍልሰታ ማክሰኞ ነው የምትገባ እና ኪዳነ ምህረት እናስቀድሳለን… ብለሽኛል፡፡ እንሄዳለን አይደል? ለፍልሰታ ብለሽ የገዛሽልኝን ቀሚሴን ልልበሰው?›› አለችኝ፡፡ ሳልመልስላት እምባየ ፈሰሰ፡፡ እምባዬን ስታይ ደነገጠችብኝ፡፡ ምን ብዬ ልመልስላት? ‹‹ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተቃጥላለች፤ ስለዚህ ቅዳሴ የለም›› ልበላት? ‹‹ማን ለምን አቃጠለው?›› ብትለኝስ ምን ልመልስላት? ‹‹እነ እገሌ አቃጠሉት›› ብዬ በልጅ አእምሮዋ ቂምና በቀል ላስተምራት? በንጹሕ አእምሮዋ ጥላቻን ልዝራባት? ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር የት ሄዶ ነው ቤተ ክርስቲያን የሚቃጠለው?›› ብትለኝ ምን ብዬ ላስረዳት? በዚህ ዕድሜዋ የሰማእትነትን ትርጉም እንዴት ልንገራት?

ቢጨንቀኝ… ‹‹ሰሞኑን ቤተ ክርስቲያን ስለሰነበትን የዚህን ዓመት ፍልሰታ አናስቀድስም፤ ቤታችንን ድመቷ ስላበላሸችብን እርሱን ስናስተካክል ነው የምንሰነብተው… እሽ ሚጣዬ?›› አልኋት፡፡ ትንሽ አሰበችና… ‹‹እሽ እማየ… ታዲያ ቄሱ መጥተው ጠበል አይረጩንም? ቤተ ክርስቲያን ስንቀር እኮ መጥተው ጠበል ይረጩናል አይደል?›› አለችኝ፡፡ ይህንስ እንዴት ልንገራት? ቄሱ ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር አብረው እንደተቃጠሉ ብትሰማ ምን ትለኝ ይሆን? ‹‹አባ ገብረ ማርያም ተገድለዋል፤ አይመጡም›› ልበላት? ለዚህች ቄስ የማይሞት መልአክ ለሚመስላት ሕፃን ምን ብዬ ነው የማስረዳት? አሁንም አለቀስሁ፡፡

ልጄ በሁኔታየ ግራ ተጋባች፡፡ ‹‹እንዴ እማዬ… በቃ ተይዋ አታልቅሽ፤ እንዲያውም መክሊት ስትመጣ ሰሞኑን ከነበርንበት ቤተ ክርስቲያን ትወስደኛለች›› አለችኝ፡፡ የአሁኑ ይባስ፡፡ ….መክሊት ታላቅ እህቷ ናት፡፡ መክሊት 16 ዓመቷ ነው፡፡ ቤታችንን ዘርፈው፣ ቤተ ክርስቲያናችንን አቃጥለው፣ ቄሶቻችንን ገድለው አልበቃቸው ያሉ አረመኔዎች ልጄን ደፍረዋት ሆስፒታል ነው ያለችው፡፡ እርሷ ወደ ሆስፒታል ስትሄድ ይህችን ሕፃን ለማትረፍ ነው ሚካኤል የተጠለልሁት፡፡ ገና ሄጄ እንኳን አላየኋትም፡፡ ጤናዋ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ አላውቅም፡፡ ያለ አባት ያሳደግኋትን ልጄን ደፈሩብኝ፡፡ አባቷ አልሻባብን ለመዋጋት ሄዶ መስዋዕት ሆኖ ከቀረ 4 ዓመት አለፈው፡፡ ሚጣ እንደረገዘች ሄዶ በዚያው ቀረ፡፡ እና ለሚጣየ… ‹‹እህትሽማ ተደፍራ ሆስፒታል ናት›› ልበላት? ‹‹መደፈር ምን ማለት ነው›› ብትለኝስ?

እውነት ካለ መንግሥት ይፍረደኝ፡፡ ሕዝብ ይፍረደኝ፡፡

—›

(ማስታወሻ፡- ይህ በምዕናብ የጻፍሁት ነው፡፡ በአእምሮዬ በዚህ ስቃይ ውስጥ ያለች አንዲት እናት በምዕናብ ተስላ እያለቀሰች ትመጣብኛለች፡፡ እረበሻለሁ፡፡ ልረሳው ብሞክርም አልሆነም፡፡ እርግጥ ከዚህ የባሰ ግፍ የተፈጸመባቸውም ይኖራሉ፡፡ እናም ሕመሜን አካፈልኋችሁ፡፡ በምዕናብ ተረብሼ ስለረበሽኋችሁ ይቅርታ፡፡ መልካም የፍልሰታ ጾም – [መላኩ አላምረው])

-›

አሁን የሆነው ሆኖ የተጎዱትን ማቋቋም ላይ ትኩረት ይደረግ፡፡ ቤት ንብረታቸው ተዘርፎ በምን ይኖራሉ… ምንግሥት ሕዝብም ተባብረን እንድረስላቸው፡፡ ዝም ብሎ ከንፈር መምጠጥ ብቻ ሆኖ እንዳያልፍ መንግሥት አንድ ሀገራዊ ኮሚቴ ያቋቁምና ያሳውቅ፡፡

(ፎቶው በትክክል ከቦታ የተነሳ ሳይሆን ነባራዊ ሁኔታውን ይወክላል ብየ የተጠቀምሁት ነው፡፡)

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew