Abiy Ahmed

ለግለሰቦች ከማጨብጨብ ባሻገር ተቋማትን እንፍጠር – የሺሀሳብ አበራ

ዶክተር አብይ እንደ ቮልት ሩጠው ግባቸውንም በሰበርዜና አፍጥነውት ነበር፡፡ ሰበር ዜናው ከሰሞኑ ርቋል፡፡ዶክተር አብይም በሁለት ሳምንታት ውስጥ እንግዳ ነገር ይዘው አልተከሰቱም፡፡ እንግዳ ነገር ብቻ ሳይሆን እሳቸውም ብዙ እየታዮ አይደለም፡፡

..

ጠሚዶ አብይ ሃገሪቱን ሊያረጋጉ የሚችሉ በርካታ ካርዶችን መዘው ተጫውተዋል፡፡ አሁን የወዲያው የመፍትሄ ካርዶች አልቀዋል፡፡

ሰበር ዜናውም እንደ ኤሊ አዝግሟል፡፡ ያለፉት ሰበር ዜናዎች የጠየመውን የህዝብ ፊት ፈገግታ የለገሱ ነበሩ፡፡ነገር ግን ዘላቂ አይደሉም፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ ሃገሪቱ ጀግና መፍጠር ታውቅበታለች፡፡ ጀግና ጀግና ሆኖ የሚቀጥልበት ተቋም እና ስራዓት ግን የለም፡፡ዶክተር አብይ ፍቅር እና መደመር እያሉ ቢሰብኩም ፍቅር የሚቀመጥበት ተቋም እና ስራዓት ስሌለ ፍቅር ሸፍቷል፡፡መደመርም በመለያየት ቦይ መፍሰሱን ይዟል፡፡

ዶክተር አብይ የሚጠቅሷቸው የለውጥ ሃሳቦችን የሚያሳፍር ስራዓት የለም፡፡ስራዓቱ በ1960ዎቹ በኮሚኒስታዊ እሳቤ የተቀለመ በመሆኑ ተሻጋሪ እና ወደ መሃል ሜዳው አስገብቶ የሚያጫውት አይሆንም፡፡ይልቁኑም ጊዜው ተቋም እና ስራዓት የሚፈጠርበት ካልሆነ በጭብጨባ አልፎ 2011 ኢትዮጲያ ብዙ ሃገር የመሆን እና የእርስ በእርስ ጦርነት ከፊቷ እንደቆመባት ከዚም ከዛም ያለው አዝማሚያ ያመላክታል፡፡

እንደ አማራ ተቋማትን መፍጠር ላይ መተኮር ይኖርበታል፡፡የአማራ እንደ ተቋሞ ጠንክሮ መቆም ኢትዮጲያን ይታደጋል፡፡ ብአዴን እንኳን ፈዛዛ እና የደነዘዘ ታሪክ ቢኖረውም በአማራ ዋጋ ኢትዮጲያን በማዳን ለሃገሪቱ ባለውለታ ነው፡፡በ 1993 የህወሓት ክፍፍልን በመድፈን፣በ2005 በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሞት የተከፋፈለውን ኢህአዲግ በመጠገን፣በ2010 የሃገሪቱ መበታተን ሊታወጅ ሲል በሽምግልናው ጠሚዶ አብይን ወደ ስልጣን በማምጣት ኢትዮጲያን ታድጓል፡፡ብአዴን ከ 2011 በኃላ በአማራ ዋጋ ኢትዮጲያን ማዳን ብቻ ሳይሆን አማራን የማዳን ስራ ይሰራ ዘንድ የመዋቅር እና የአደረጃጀት ክለሳ እያደረገ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ብአዴን የአንድ ወገን የበላይነትን ቀድሞ በግለሰብ ደረጃ ቢሆንም ተቃውሟል፡፡እንደ ፓርቲ ከብአዴን የለውጥ ሃይሎች የሚቀድም የለውጥ አመላካች አልነበረም፡፡ነገር ግን ከላይ የተቀመጡት ጥገኛ እና ተላላኪ የብአዴን መሪዎች የለውጥ ሃይሎችን ተፈታትነው ባይጥሏቸውም ከጉዟቸው ገቷቸው፡፡ ብአዴንም የሚመራውን ህዝብ መስዋዕትነት ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ቀጣይ ነሃሴ መጨረሻ የሚካሄደው ጉባዔ የለውጥ ሃይሎች ከፓርቲ መመሪያ ወጥተው መሪ ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ብአዴን በቀጣዮ ጉባዔ ካልታደሰ የሚመራው ህዝብ ያጠፋዋል፡፡ብአዴንም ፍፁም አምባገነንን ሊሆን ይችላል፡፡በቀጣዮ ጉባዔ መሰረታዊ ለውጥ ካላደረገ በመሳሪያ መግዛት አማራጭ አድርጎ ሊወስድ ይችላል፡፡በሃገር ደረጃም ሁሉም አጋር ድርጅቶች ወደ ተቀራረበ የዲሞክራሲ መስመር ካልተጓዙ ከትናንቱ የበለጠ አምባገነናዊነት ሊመጣ ይችላል፡፡ነገር ግን ህዝቡ አምባገነናዊነትን የሚሸከም ትክሻ የለውም፡፡ በዚህ መሃል ሁከት መፈጠሩ ሩቅ ግምት አይሆንም፡፡

የሲቪክ አደረጃጅቶች ማጠናከር፣ብአዴን እየተከታተሉ መደገፍ መተቸት፣በመቅረብ እና በመሳተፍ ወደ ለውጡ መግፋት ያስፈልጋል፡፡

ጊዜን ተጠቅሞ የአማራ ወጣቶች ፣ምሁራን፣ሽማግሌዎች፣ሃኪሞች ወዘተ እያሉ በማደራጀት የአማራን ብሄርተኝነት ተቋማዊ ቅርፅ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ከሳይቨሩ ንትርክ ወጥቶ መሬት ላይ መደራጀት እና መናበብ፣መወያየት እና መጠያየቅ ያስፈልጋል፡፡

..

አሁን አንፃራዊ ነፃነት ስላለ የአክቲቪዝም ስራ ወደ መሬት ማውረጃ ጊዜ ነው፡፡ይህች ወር ካለፈች እንደ 1966 ቱ እና 1983 ቱ የከሸፈ አብዮት ሆኖ የብዙ አስርት ዓመታትን ዕዳ ወቅቱ አሸክሞን ሊያልፍ ይችላል፡፡ታሪክ ራሱን በመጥፎ ገፅታው እንዳይግመው የለውጡን ጊዜ ለመጠቀም ትርፍ ጊዜ የለም፡፡

በነጠላ ጉዳዮች እና በፊስቡክ ኮሜንት እየተበሻሸቁ ወሳኙን የድል ምዕራፍ ከማሳለፍ ይልቅ መሬት ላይ ነጥብ የምታህል ተተግባሪ ነገር መከወን ወቅቱ ይጠይቃል፡፡

እስካሁን የአማራ በጎ አድራጎት ድርጅት፣የአማራ የምሁራን ጉባዔ፣የአማራ የወጣቶች ማህበር የመሳሰሉት የሲቪክ አደረጃጅቶች እየተዋቀሩ ነው፡፡ይህ በሌሎችም ዘርፎች ሊቀጥል ይገባል፡፡

..

እንደ ወቅቱ ተቀያያሩ ሆኖ ብአዴን እና አብንን እንደሚገባቸው እና እንደሚያስፈልጋቸው መደገፍ ያስፈልጋል፡፡የብአዴን መጠንከር የአብን ዕድል ያደረጃል፡፡የአብን መጠንከር ብአዴንን ያነቃል፡፡ብአዴን እና አብን ኢ ተነጣጣይ ህልውና ለጊዜው አላቸው፡፡ከሁለት ዓመት በኃላ ደግሞ ለተሻለ የህዝብ የሚጠቅመው ሁሉ ይመረጣል፡፡ እስከዛው ግን የሁለቱም መጠንከር የነፃነትን መንገድ ያቀርቡታል፡፡

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew