ሰላዩ ባሻ አዋሎም (ባሻይ ኣውዓሎም) – ለአድዋ ድል ትልቅ ድርሻ የተወጡ ኢትዮጵያዊ ጀግና !

እንካ የሀገር ጀግና – እንካ ባለውለታ ተኩሶ ብቻ ሳይሆን – ሰልሎ ጠላት ሚመታ ! . የአድዋ ድል ሲነሳ የባሻ አዋሎምን ድርሻ አለማስታወስ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ እኚህ ጀግና በስለላ የተጫወቱት ሚና አንድ ጀግና አርበኛ ተኩሶ በመግደል ካደረገው ድርሻ ከፍ ቢል እንጅ አያንስም፡፡ ‹‹ለመሆኑ ምን ሠርተው ነው?›› አልህ? ተከተለኝ…… በል በስማቸው የታተመውን መጽሐፍ ፈልግና አንብብ – ምን አልባት ገበያ ላይ ካለ፡፡ እኔ በጥቂቱ ጀግናችንን ላስተዋውቅህ፡፡ የአድዋ ጦርነት ከመካሄዱ አስቀድሞ ጠላት (ጥልያን መሆኑ ይገባሃል) የኢትዮጵያን የጦርነት ምሥጢር ለማወቅ በቁጥር የበረከቱ ሰላዮችን አሰማርቶ ነበር፡፡ አይ ፈረንጅ… መቼም ተንኮሉ አይቻልም፡፡ የእኛ የዋሐን አርበኞች ሚተነፍሷትን ሁሉ እየለቃቀሙ ለጥልያን ጀኔራሎች ወሬ ያደርሱ ዘንድ ከተቀጠሩት ሰላዮች መካከል ደግሞ አንዱ ባሻ አዋሎም ነበሩ፡፡ (በሻን አላዋቀቻውማ ይሄ ሰላቶ)፡፡ ደግሞ እኮ የጣሊያን መንግስት መረጃ አቅራቢ (ሰላይ) አድርጎ ከመደባቸው መካከል እንደ ባሻ የሚያምነው ሰው አልነበረውም አሉ፡፡ ተሸወድ ሲለው እኮ ነው – በእርሱ ቤት በነባሻ መረጃ አቅራቢነት የምኒልክን ሠራዊት አዘናግቶ ጉድ ሊሠራን ነበር፡፡ ይሄ ጉዳም ! ጀግናው አውዓሎም ግን የሀገር ፍቅር በልባቸው ተቀብሮ ነበርና ይሄንን በጥልያን ሰላቶዎች የመታመናቸውን አጋጣሚ ለሀገራው ተጠቀሙበት፡፡ ከስንት ባንዳ መሐል (በወቅቱ በትክክልም ሀገር ክደው መረጃ እያወጡ ለጠላት ሚሰጡ መኖራቸውን ከዘነጋህ ተሸደሃል – የእናት ሆድ ዥንጉርጉርም አይደል) ባሻ አውዓሎም ለኢትዮጵያም መስራት ጀመሩ፡፡ (ዕድሜ ይስጣቸው ልል ነበር ዐርፈዋል….. ነፍሳቸውን ያጽድቃት!!!) የጦርነቱ ጊዜ እየተቃረበ ሄደ፡፡ ባሻይ ሆዬ ለድል ቋመጡ፡፡ ይሄንን ምደረ ሰላቶ ጉድ የሚሰሩበትን ቀን ናፈቁ፡፡ ለጥልያን የተሳሳተ መረጃ እየሰጡ አዘናጉት፡፡ ስላመናቸው አልተጠራጠራቸውም፡፡ በአንጻሩ እያንዳዷን የጥልያንን የጦርነት ስልትና ምክር ሳይቀንሱ ሳይጨምሩ ለአጤ ምኒልክ እና ለእቴጌ ጣይቱ በምሥጢር ተናገሩ፡፡ በጋራ መከሩ፡፡ የተማከሩት ነገር መቼም መልካም ነው… አንድ መለኛ ዘዴ ብልጭ አለላቸው፡፡ የጋራ ምክራቸውም ይህ ነበር፡፡ ‹‹የካቲት 23 ቀን በሰንበት ላይ ጊዮርጊስ የተደራረበ በዓል ነውና… ንጉሡም መኳንንቱም ይህንን ዕለት በቅዳሴ ለማክበር ወደ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳሉ፡፡ ከሰራዊቱም መሐል ግመሹ ሰንበትን አክባሪ ሌላውም ቀለብ ለመፈለግ በየመንደሩ የሚሄድ በመሆኑ፤ በዚህ ጊዜ ምኒልክ እና ጣይቱን በቀላሉ ይማረካሉ›› በማለት ባሻይ አውዓሎም ጄኔራል ባራቴሪን እንዲያሳምን ተደረገ፡፡ ጀግናው አዋሎምም ይሄንን ወስደው በነገር ሁሉ ለሚያምናቸው ጀኔራል ባራቴሪ ነገሩት፡፡ ጅሉ ጄኔራልም የአውዓሎምን መረጃ በመቀበል ወዲያው ለሰራዊቱ ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡ ለየካቲት 23 ጦርነት እንዲዘጋጅ፡፡ የተወሸደ ጄኔራል የመራው ምድረ ሰላቶም (የጥልያን ጦር) አንድ ሳይቀር ተለቃቅሞ የካቲት 22 ቀን ከምሽግ ወጣ፡፡ (ወይ የተደገሰለትን አለማወቅ!) ይህ የጥሊያን ጦር እንቅስቃሴም ወዲያው ለአጤ ምኒልክ በመልዕክተኛ ተነገራቸው፡፡ በደንብ ተደራጅተውና መሽገው ጠበቁታ፡፡ ‹‹አይ ጥልያን ሞኙ – ሰው አማኙ››… ሁሉም ለጥቅሙ ሚያድር ባንዳ መስሎት ተሸወደ – የታባቱ፡፡ ባሻዬ ጉድ ሰሩልኝ ይሄንን ነጫጭባ፡፡ አይነጋ የለም የካቲት 23 ነጋ፡፡ የልባቸውን በልባቸው የያዙት ባሻይ አውዓሎም (ጥርሳቸውን እንደነከሱና አንዳንዴም የማስመሰል ፈገግታ እያሳዩ ይመስለኛል) የጣሊያንን ጦር እየመሩ ከፊት ከፊት የኢትዮጵያ አርበኞች ወደ መሸጉበት ቦታ ወሰዷቸው፡፡ ጥልያን የሚያውቀው ምንሊክና ሠራዊቱ ቅዳሴ ላይ መሆናቸውን ነው፡፡ (በዚህች ዕለት የሚቀደሰውም መስዋእቱም እርሱ መሆኑ አልገባውማ)፡፡ ባሻ አዋሎም የሚመሩት የጥልያን ጦር ልክ የኢትዮጵያ ጦር የመሸገበት ቦታ ደረሰ፡፡ (ጉድ መጣ…!) አሁንም ለጥልያን ሀገሩ ሰላም ነው (ሰላም ይንሳውና)፡፡ ባሻ በሀበሻ ወኔ ፎከሩ፡፡ ጥልያን ደስስስ አለው፡፡ ‹‹የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ ይሉሃል ይሄ ነው›› ብሎ ተረተ – በባሻ ጎራዴ የሀበሻን አንገት ሊያስቆርጥ እኮ ነው በእርሱ ቤት (አልሰሜን ግባ በለው!)፡፡ ወዲያው ባሻ ጎራዴያቸውን ወደ ጥልያን ሰላቶ አዞሩታ፡፡ ምድረ ነጫጭባ ሰማይ ምድሩ ዞረበት፡፡ ከዚያማ ምኑ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያዊ አርበኛ ከየመሸገበት ጉድባ እየፎከረና እየተንደረደረ በጥልያን ላይ መዓት አወረደበት፡፡ ድሉም የእኛ ሆነ !!! ደግሞ የባሻ እድለኛነታቸውስ አይገርምም… ጀግናው አውአሎም በጦርነቱ አልሞቱም፡፡ ለፈፀሙት ታላቅ የሀገር ውለታ የእንጥጮ ወረዳ አስተዳዳሪ ሆነው ተሾመውም ነበር፡፡ ሲያንሳቸው ነው!!! እንዳከበሩን ነፍሳቸው ትክበር!!! … ማስታወሻ፡- ባሻ አውዓሎም ሀረጎት በ1844 ዓ.ም በትግራይ ክልል አደዋ እንጥጮ ወረዳ ተወለዱ (ይለናል ስለእርሳቸው የተጻፈው የታሪክ ክታብ)፡፡ የራስ አርአያ ድንቅ ወታደርም ነበሩ፡፡ በልጅነታቸው ራስ አርአያ በመተማ ጦርነት ሲሞቱ አውዓሎም የራስ መንገሻ አሽከር ሆኑ፡፡ የባሻነት ማዕረግ የሰጧቸውም ራስ መንገሻ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ባሻ አውዓሎም በተወለዱ በ78 ዓመታቸው ህዳር 12 ቀን በ1922 ዓ.ም ባደረባቸው ህመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ነፍሳቸውን ከጻድቃን ይደምርልን !!! —————-/› ——–/› እስኪ በዚህች የድል ቁንጮ በምትሆን የአድዋ በዓል በሚዘከርበት ወቅት እንኳን በበሬ ወለደ የፈጠራ ትርክት የጀግኖችን ስም ከማጉደፍና ለአንድነት ተጻራሪ ሆኖ ከመቆም እንውጣና ለሀገርም ለትውልዱም የሚበጀውን እናውጋማ፡፡ ይህችንን በአባቻችን የሕይወት መስዋእትነት የተገኘች፣ ከከዋከብት በላይ የምታሸበርቅ፣ ከጨረቃም ከፍ ብላ የምትደምቅ፣ ከፀሐይም ይልቅ ለውስጣችን የምታበራ ድል በጥላቻ ከተሞላው ልባችን በሚገሳ የከፋፋይ ቃላት እየመረዝን ክብሯን ለማደብዘዝ ከመጣር ይልቅ የድሉን ተወርዋሪ ከዋከብት እንዘክር፡፡ ትውልዱም የሀገር ፍቅርን ጥግ ይረዳ፡፡ ለዳር ለነጻነት የሚከፈለው ዋጋም እስከምን እንደሆነ ይገንዘብ፡፡ ዛሬ የምንኩራራበት የድል ቀንና የወረስናት ነጻ ምድር እንዲሁ የተገኘች ናት ብሎ እንዳይዘናጋ የተከፈለለትን ዋጋ እንንገረው፡፡ ይህ ነው የሚበጀው፡፡ በአላዋቂነታችን ላይ ጥላቻን ደርበን የሆነውን እያጣመምን ያልሆነውን እየፈጠርን ለእኛ ፖለቲካዊም ሆነ ሌላ ትርፍ ስንል ብቻ ትውልዱን አናወናብደው፡፡ (ለነገሩ ድከሙ ቢለን እንጅ እንኳንስ ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘውን አድዋንና የድሉን ባለቤቶች ቀርቶ በአንዲት መጽሐፍ ብቻ የተቀመጠችን እውነተኛ ታሪክም በፈጠራ ትርክት ማደብዘዝ አንችልም፡፡) ‹/—————-/›

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew

Leave a Reply

Your email address will not be published.