ሰይጣን ባንች እንዴት አይቅና !?!

ሰይጣን ባንች እንዴት አይቅና !?!

ሰይጣን ባንች እንዴት አይቅና !?!

(መላኩ አላምረው)

የሰማይ ብርሃን ፍንጣዊ – የወረደበት ከሰማይ

የዚያ ተራራ ምሳሌ – የታቦር ኮረብታሽ ከላይ…

.

የፍቅር ሐይቅሽ ከስር – የንጉሥ ማሕተም ከመሐልሽ

በተፈጥሮ የተቸረሽ – – – በጥበብ የተሳለልሽ…

.

ኢትዮጵያዊ በአንድነት – ብሔር ከብሔር ተፋቅሮ

ሰሜን ከደቡብ ተጋብቶ – ምሥራቅ ከምዕራብ ተማክሮ

በልዩ የእምነት መዝሙር – በልዩ የባህል ሕብር

ከነፍስ በሆነ ትስስር – ከልብ በሆነ ትብብር

ልዩነቱን ውበቴ ብሎ – ሲኖርብሽ ዓይኑ ዓይቶ

ሰይጣን እንዴት አይቅና – ይቃጠል እንጅ እንቅልፍ አጥቶ!

የቃየልን እጅ በአቤል ላይ – በክፋት ያስነሳ ሰይጣን

ልጆሽን እርስበርስ – እያደማማ ቢቀጣን….

እንግዳ ነገር አይደለም – ይሄ ምኑ ይገርማል?

ወንድም ወንድሙን ሲገድል – እርግጥ ነው በእጅጉ ያማል!

እርግጥ ነው ሰላም ይነሳል – አካል ከመንፈስ ያደማል።

.

ሐዋሳ የፍቅር ደሴት – ሐዋሳ የሕብር አድባር

ሐዋሳ የደስታ ደሴት – ሐዋሳ ለዓይን ውበት ገባር

ሐዋሳ የአብሮነት ቅኔ – ሐዋሳ የአንድነት ቅመም

ዲያብሎስማ ተንኮል ይሥራ – ልጅሽ በልጅሽ ይታመም 😞

.

የሰሜኑ ሊቅ ቅኔ – የደቡብ ካህን ቅዳሴ

የምሥራቁ ሼህ አዛን – የምዕራቡ ውዳሴ

በሕብር እየተዜመ – በአንድነት እየተሰማ

ዘንዶው እንዴት አይቀና – ይቃጠል እንጅ ባንችማ !

.

በሥላሴ ተባርከሽ – በገብርኤል ክንፍ ስትከለይ

ድምጽሽ ሰማይን ሲያንኳኳ – በየመቅደሱ ስትጸለይ

በየመስጊዱ ዱዓ – በአዛንና መንዙማ

በየደብሩ ሰዓታት – በሰንበት ተማሪ ዜማ

ስምሽ በፍቅር ሲጠራ – ከጠፈር በላይ ሲሰማ

ከይሲ ዝም ሊል አይችልም – ያቃጥለዋል ይህማ!

የብዝኃ ባሕልሽ ሕብር – የድንቅ ተፈጥሮሽ መስህብ

ታናሿን ኢትዮጵያ ስሎ – ውበትሽ ዓለምን ሲስብ

ታሪክ ባሕልሽ ተጠንቶ – ልዩ ጥበብሽ ተመርምሮ

ጨምበላላሽ በቅርስነት – ሲሄድ ባሕርን ተሻግሮ…

ዝናሽ ዓለምን ሲናኝ – ፍቅርሽ ሁሉንም ሲጠራ

ከይሲ በዚህ ተናዶ – እንዴት የዘር ጥል አይዘራ ? 😞

.

የአዳምና የሔዋን – በገነት መኖር የሚያስቀናው

የቃየል እጅ የአቤልን ደም – ማፍሰሱ የሚያጽናናው

በውብ ገነትነትሽ – ሕዝብሽ በፍቅር ሲስማማ

ሰይጣን መቅናቱን ትቶ – መልአክ ሊሆን አይችልማ !!!

.

ተጨማሪ ደም እንዳይፈስ – ሕዝብሽ ከገነት እንዳይወጣ

ከይሴ በሥላሴ ይገሠጽ – በገብርኤል ሰይፍ ይቀጣ !!!

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew