በመፋቀራችን፦ ጌታ ቅር አይለውም፤ አላህ አይከፋውም።

በመፋቀራችን፦ ጌታ ቅር አይለውም፤ አላህ አይከፋውም።

በመፋቀራችን፦

ጌታ ቅር አይለውም፤

አላህ አይከፋውም።

(መላኩ አላምረው)

—***—

መግቢያ፦

ከመካ ቀጥለን፣

ከአፍሪካ ቀድመን፤

በክርስቲያን አምባ፣ መስጊዱን አቁመን፤

እስላም ክርስቲያኑ፣ በአንድ ላይ ከትመን፡፡

በዓላችሁ በዓላችን፣ በዓላችን በዓላችሁ፤

ደስታችሁ ደስታችን፣ ደስያችን ደስታችሁ፤

ሆኖ የጠበቀን፣ ከአበው የወረስነው፤

ኢትዮጵያዊነት! – መለያችን ይህ ነው።

-*-

ሀተታ፦

በእውነት ከሆነ…

በእኛ የደስታ ቀን፣ የእናንተ መንዙማ፤

በእናንተም በዓላት… ያሬዳዊ ዜማ፤

(ለአምልኮ ሳይሆን፣ ለፍቅር ቢሰማ፤)

ጌታ ቅር አይለውም፣ አላህ አይከፋም፤

ጽድቅ በክፋት እንጅ፣ በፍቅር አይጠፋም።

የጽድቅን አኗኗር፣

አዛባነው እንጅ፣ እያበዛን ጣጣ፤

በሰው ልጆች ዓለም፣

ከፍቅር የሚሻል፣ ጽድቅ ከየት ሊመጣ?

.

ምንም ጽድቅ ያለ-እምነት፣ ሊታሰብ ባይችልም፤

ያለ-ፍቅርም እምነት፣ ቅዠት ነው ከንቱ ህልም።

.

እኛም በእኛ እምነት፣ እናንተም በእናንተ፤

መንግሥቱን ለመውረስ፣ ልባችን ከሻተ፤

እምነታችን “በሩ”፣ ቢሆንም ባይሆንም፤

መንገዳችን ገነት፣ ከቶ አያደርሰንም፡፡

ፍቅር የሌለንን፣ ፈጣሪ አያውቀንም፡፡

ምክንያቱም፡-

ዘላለም ሚገዛው፣ ዓለማትን ፈጥሮ፤

ፈጣሪ ፍቅር ነው! ለፍቅር የፈጠረን፣ በፍቅር ቀምሮ፡፡ (ፍቅርን ያለ ፍቅር፣ ለማግኘት ሙከራ፤

ይህ ከንቱ ድካም ነው፣ የሰነፎች ሥራ፡፡)

.

በእኛ መጽሐፍ ቅዱስ፡-

‹‹ሁሉም ነገር ባንተ፣ በፍቅር ይሆን ዘንድ፤

አይደለም ወዳጅህን፣ ጠላትህ ውደድ፡፡››

የሚል ትዕዛዝ አለ!

ትርጉሙም ምሥጢሩም፣ ‹‹ፍቅርን›› ያከለ፡፡

የፍቅርን አስገኝ – ‹‹እ ር ሱ ን›› የመሰለ፡፡

.

በእናንተ ቁርዓንም፡-

‹‹እንኳንስ ለሰው ልጅ፣ ለፍጥረቱ ሁሉ፤

ራርታችሁ ኑሩ፣ እደሩ እንደ ቃሉ፡፡››

ተብሎ የተጻፈ፣ የፍቅር ቃል አለ፤

ክርስቶሳዊውን፣ የእኛን የመሰለ፡፡

.

መደምደሚያ፦

ፍቅር ከሆነ አምላክ፣ ለሰው የተሰጠ፤

ምንም ትዕዛዝ የለም፣ ከፍቅር የበለጠ፡፡

እኛ ስንዋደድ፣ ዓይኑ ደም ሚለብስ፤

ልባችን ሲፋቀር፣ እግሩ የሚያነክስ፤

ሰይጣናዊ ፍጡር፣ ከሰው ልጅ ባይጠፋም፤ በመፋቀራችን…

አላህ ቅር አይለውም፣ እግዚአብሔር አይከፋም፤

ጽድቅ በክፋት እንጅ፣ በፍቅር አይጠፋም፡፡

~~~~//~~~~

~//~

(መላኩ አላምረው ~ #ነፍጠኛ_ስንኞች)

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew