አማራ ክልል እና ጤና (የሺሐሳብ አበራ)

በአማራ ክልል፡-

• አንድ ሆስፒታል ለ1.2 ሚሊዮን ህዝብ ያገለግላል፤ ተጨማሪ 210 ሆስፒታሎች ያስፈልጋሉ

• አንደኛ በተባለው ክልል ግን አንድ ሆስፒታል ለ46 ሺህ ህዝብ ብቻ ያገለግላል

በኩር ሕዳር 24/2011ዓ.ም፦ የጤና ተቋማትና አማራ ክልል

በአማራ ክልል የጤና እንቅስቃሴ ዙሪያ የዳሰሳ ጥናት ያደረጉት ዶክተር አንድነት አዱኛው ሰሞኑን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በተሳታፊነት ተገኝተው ነበር :: በዚህ ወቅት በክልሉ ያለው ሆስፒታል እና የህዝብ ቁጥር ጥምረት በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ነግረውናል:: አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በአማራ ክልል ለአንድ ነጥብ 2 ሚሊዮን ህዝብ ያገለግላል ይላሉ:: ይህ አኃዝ ከትግራይ ክልል (አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል 45 ሺህ 996 ህዝብ ይገለገላል) ጋር ሲነጻጸር በ27 እጥፍ የአማራ ክልል ያንሳል፤ ከአማራ ክልል አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ከሚገኘው ደቡብ ክልል ደግሞ በ2 ነጥብ 2 እጥፍ ያንሳል:: ይህ ማለት ብዙ በሽተኞች በጥቂት ሆስፒታሎች እንዲታከሙ ይገደዳሉ ማለት ነው:: በሽተኞች አጣዳፊ ህመም ታመው ወረፋ ይጠብቃሉ:: በሀገሪቱ ከፍተኛ ወረፋ ያለባቸው ሆስፒታሎችም በአማራ ክልል የሚገኙት ናቸው::

ዶክተር አንድነት ችግሩ የሆስፒታል እና የህዝብ ቁጥሩ አለመጣጣም ብቻ አይደለም ይላሉ:: ዋናው ችግር የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት አለመሟላቱ ጭምር እንጅ::

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አ.እ.አ 2016 (SARA 2016) ባወጣው ጥናት የተቋማት አገልግሎት እና ዝግጁነት (አማራ ክልል ካሉት የህክምና ተቋማት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት የሚሰጡት 54 ከመቶው ብቻ ናቸው:: ይህም የአማራ ክልል በመጨረሻው ረድፍ በዘጠነኛነት ደረጃ እንዲቀመጥ ያደርገዋል ይላሉ::

ዶክተር አንድነትም የኢትዮጵያን የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ጥናት ዋቢ አድርገው አብነት ያነሳሉ:: የሀገሪቱ የህክምና አልጋ እና የታካሚ ቁጥር ንጽጽር ሲታይ 92 አልጋ ለመቶ ሺህ ህዝብ ያገለግላል:: ይሁን እንጂ በአማራ ክልል 20 አልጋዎች ለ100 ሺህ ህዝብ አገልግሎት ይሰጣሉ:: ይህም ማለት የአማራ ክልል ከሀገሪቱ ጥቅል በአልጋ እና በታካሚ ምጥጥን ከአራት እጥፍ በላይ ወደ ኋላ ቀርቷል:: በሌላ አነጋገር በአማራ ክልል የሚታከሙ ህሙማን አልጋ ይዘው መታከም አይችሉም ማለት ነው:: መሬት ላይ መተኛት ወይም አለመታከም አማራጫቸው ሊሆን ይችላል:: በዚህ ውስጥ ሞት ነጻ ፈቃድ ያገኛል::

በጤና ጣቢያዎች የቤተ ሙከራ እና የምርመራ መሳሪያዎች አቅርቦት ከፍተኛው ክልል 77 በመቶ ሲያሟላ አማራ ክልል ግን 31 በመቶ ብቻ አሟልቷል:: ይህም አማራ ክልል ከከፍተኛው ክልል በሁለት ነጥብ አምስት በመቶ እጥፍ ያንሳል:: የሀገሪቱ 35 በመቶ ሲሆን፤ የአማራ ክልል ከጥቅል ሀገሪቱ አራት በመቶ አንሶ ይገኛል::

በሌላ በኩል በጤና ጣቢያዎች ሊኖሩ ከሚገባቸው መድሃኒቶች ውስጥ መስፈርቱን የሚያሟሉት 50 በመቶ ብቻ ናቸው:: በዚህም የአማራ ክልል ከዘጠኝ ክልሎች እና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በ10ኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል:: መሰረታዊ በሚባሉ መድሃኒቶች አቅርቦትም የአማራ ክልል ዝቅተኛ ነው:: በእናቶች እና ህፃናት የድንገተኛ አገልግሎት ዝግጁነት ከክልሎች ከፍተኛው 82 በመቶ ሲሆን አማራ ክልል 68 በመቶ ላይ ወርዶ ይገኛል::

በኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የህብረተሰብ ጤና አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ክርስቲያን ታደለ እንደሚገልፁት ደግሞ የአማራ ክልል እናቶች በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ለመሄድ በአማካኝ 128 ደቂቃ ይወስድባቸዋል:: አንዳንድ ክልሎች ደግሞ በአማካይ 30 ደቂቃ ብቻ ይጓዛሉ:: በዚህ ስሌት አንድ የአማራ እናት ምጥ ተይዛ ከሌላው ክልል በአራት እጥፍ( ሁለት ስዓት) መንገድ ለመጓዝ ትገደዳለች:: በዚህ መንገድ ውስጥ ሞት እና የሚወለደው ልጅ የጤና እክል ያጋጥመዋል:: የዚህ መሰረታዊ ችግሩ የአማራ ክልል በመንገድ መሰረተ ልማት ወደ ኋላ መቅረቱ እና የጤና ጣቢያ ተደራሽነት አናሳ መሆኑ ነው ብለዋል::

ከ2006 እስከ 2016 የዓለም ባንክ በኢትዮጰያ የተካሄደውን የልማት ጉዞ በተነተነበት ሪፖርቱ እንዳረጋገጠው አማራ ክልል በመንገድ እና በመብራት ብሎም በሌሎች መሠረተ ልማቶች ከሁሉም ክልሎች የመጨረሻ ደረጃ ላይ ይቀመጣል:: ይህ ደግሞ የጤናውን ዘርፍ በእጅጉ ጐድቶታል::የዓለም ባንክ የሀገሪቱ እድገት ፍትሃዊነት የጎደለው እንደሆነ በሪፖርቱ ያረጋገጠ ሲሆን፤ በኢፍትሃዊነቱ ከፍተኛ ተጠቂ ደግሞ የአማራ ክልል ነው::

አቶ ክርስቲያን እንደሚያስረዱት ሀገሪቱ አንድ ጤና ኬላ ከሶስት ሺህ እስከ አራት ሺህ ህዝብ እንዲያገለግል አድርጋ ብትቀርጽም፣ በአማራ ክልል ግን አንድ ጤና ኬላ ከሰባት ሺህ እስከ 12 ሺህ ህዝብ እንዲያገለግል ሆኗል:: የአማራ ክልል ታዳጊ ክልሎች ከሚባሉት ሁሉ በጤና መሠረተ ልማት ወደ ኋላ ቀርቷል ይላሉ ::በጤናው ዘርፍ ባለው ኢፍትሃዊነት ምክንያት ባንድ ክልል አካባቢ አይዮዲን 98 ከመቶ ደርሶ የሀገሪቱ የአይዮዲን ጨው ስርጭት 4 ከመቶ ብቻ ሆኖ እንደነበርም አቶ ክርትስቲያን አውስተዋል::

ጤና እና ምጣኔ ሀብት

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከ60 ሺህ እስከ 100 ሺህ ዜጎችን ተደራሽ ያደርጋል:: ይሁን እንጂ ይህ የሆስፒታሎች የተደራሽነት ምጥጥን በአማራ ክልል መልኩ የተለየ ነው:: በክልሉ የሚገኙ የሆስፒታሎች ብዛት 80 ብቻ ሲሆኑ እነዚህን ለ100 ሺህ ዜጎች ተደራሽ ይደረጉ ቢባል በክልሉ ተጨማሪ 210 ገደማ ሆስፒታሎች ያስፈልጋሉ ማለት ነው::

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ብርሃኑ ሲሳይ የአማራ ክልል በጤና አጠባበቅ ዘርፍ ወደ ኋላ መቅረቱ ልማትን ወደኋላ ይገፋዋል ይላሉ::

ዶክተሩ እ. ኤ. አ.2017 በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የተደረጉ ጥናቶች ዋቢ አድርገው እንደገለፁት የአማራ ክልል በአንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚገለገለው የህዝብ ብዛት አንድ ሚሊዮን 218 ሺህ 844 ሲሆን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች 564 ሺህ 059፣ በኦሮሚያ 222 ሺህ 050 እና በትግራይ 45 ሺህ 996 ነው ።

“ጤናውን ያልጠበቀ ማህበረሰብ ልማት ላይ አይገኝም:: ጤናውን ለመጠበቅ ሲል ያለውን አንጡራ ሀብት በመሸጥ ለህክምና ያውላል:: ይህ ትውልድን እንደ ማቀጨጭ ይቆጠራል” ይላሉ ዶክተር ብርሃኑ:: ዶክተር ብርሃኑ “የአማራ ክልል በጤና አጠባበቅ ዘርፍ ዝቅተኛ መሆኑ የአማራ ህዝብ ለራሱም ሆነ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ማበርከት የሚጠበቅበትን ያህል እንዳያበረክት ሆኗልም” ብለዋል::

የችግሩ ምንጭ

ዶክተር አንድነት አዱኛው የፌዴራሉ መንግስት በአማራ ህዝብ ላይ ኢ-ፍትኃዊ አሰራር መዘርጋቱ የጤናውን ዘርፍ ጐድቶታል ይላሉ:: ከ1983 ዓ.ም ወዲህ የተዘረጋው አማራ ጠል የሚመስለው የዘውግ ፖለቲካ አማራን በተቋም ደረጃ ጐድቶታል:: ለዚህ ማሳያም አንዱ የጤናው ዘርፍ ነው ብለዋል::

በሌላ በኩል ደግሞ የክልሉ መንግስት ቸልተኝነት ለችግሩ መንስኤ ነው የሚሉት እርሳቸው የክልሉ መንግስት የሚገባውን አለመጠየቁ ይልቁንም በውሸት ሪፖርት የሌለውን አለኝ ማለቱ የክልሉን የጤና እንቅስቃሴ ጐድቶታል:: ህብረተሰቡን ሳይሆን አለቆችን ለማስደሰት የሚያጐበድድ አመራር መኖሩ፤ የአማራን ህዝብ ተጐጅ አድርጐታል:: የተንዛዛ ቢሮክራሲ፣ የጤና ባለሙያዎች አያያዝ ድክመት መኖሩም የጤናው ዘርፍ እንዲቀጭጭ አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል::

መፍትሔ

አቶ ክርስቲያን ታደለ የአማራ ክልል በጤናው ዘርፍ ከኋልዮሽ ጉዞው ለመመለስ ከፌዴራሉ መንግስት ካሳ ከማስፈለጉም በላይ፤ የራሱ የስነ ህዝብ ፖሊሲ ሊኖረው ይገባል ባይ ናቸው::

የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ም/ሀላፊ አቶ ብዙአየሁ ጋሻው “አዎ ባይ” አመራር ብቻ መኖሩ ክልሉን እንደጐዳው ጠቅሰው ይህን ማስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል:: “ችግሩ ከኛው ከራሳችን የሚመነጭ ነውም” ብለዋል:: ይሁን እንጂ ወደ ኋላ የቀረንባቸው እንዳሉ ሁሉ የቀደምንባቸው ዘርፎችም አሉ ያሉት አቶ ብዙየሁ ለአብነት የጤና መድህን አገልግሎትን ጠቅሰዋል ::

የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባው ገበየሁ በበኩላቸው “ችግሩን ለማስተካከል እንሰራለን” ያሉ ሲሆን፤ በአንዳንድ ዘርፎችም የፌዴራሉ መንግስት ድጎማ እንዳደረገ ተናግረዋል:: የውሸት ሪፖርትን መቆጣጠር እና በጎደለው ለመሙላትም ቢሮው እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል::

በአማራ ክልል በምክትል በርዕሰ መስተዳድር ደረጃ የማህበራዊ ዘርፍ እና የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በጥናት ላይ ተመስርተን በመስራት ለፍትኃዊ ተጠቃሚነት እንቆማለን ብለዋል:: የኢ-ፍትኃዊ ጉዳይ ያለፉት ዓመታት የመንግስታዊ መዋቅራት መገለጫ እንደነበርም አስታውሰዋል::

በኩር ሕዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም ዕትም

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew