Ethiopian Flag

አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ሰንደቅ ዓላማችንና ባንዲራቸው!

(መላኩ አላምረው)

ከኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካ ሀገራትን ‹‹የአረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ››ን የሰንደቅ ዓላማ ቀለማት አመራረጥና ታሪካዊ አመጣጥ ስንዳስስ…. በሀገራችን ታሪካዊትነትና የነፃነት ዓርማነት ኩራት ይሰማናል፡፡
እነዚህ የእኛ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት (አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ) ‹‹የፓንአፍሪካኒዝም ቀለማት›› ተብለው እንደሚጠሩ እናውቅ ይሆን? በሉ ከዛሬ ጀምሮ እንወቅ፡፡ እነዚህ ሦስቱ ቀለማት ‹‹የፓንአፍሪካኒዝም ቀለማት›› የመባላቸውም ሆነ ለአፍሪካ ሀገራት ሁሉ የነፃነት ምልክት ሆነው የመታየታቸው ምሥጢር ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያ›› ናት፡፡ ‹‹ለምን ኢትዮጵያ?›› ብለን ስንጠይቅ ደግሞ ጉዳዩ ከዐድዋ ድል ጋር ተያይዞ እናገኘዋለን፡፡ ኢትዮጵያዊው የዐድዋ ድል በነጭ ያለመገዛት፣ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ (ከአፍሪካም ውጭ ላሉ ጥቁሮች) ኩራትና የነፃነት ምልክት ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በዓለም ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ እንደ ዐድዋ ድል ያለ የነፃነት ምልክት የለም፡፡
በኢትዮጵያ ምድር በኢትዮጵውያን ደም የተገኘው የዐድዋ ድል ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁር ነጭን ማንበርከክ እንደሚችል ያሳዬ ትልቅ ምልክትና ዓርማ ነበርና በተለይም አፍሪካውያን የኢትዮጵያን ዓርማ ዓርማቸው ማድረግን መረጡ፡፡ በየሰንደቅ ዓላማቸውም በሙሉም ሆነ በከፊል አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ቀለማትን መጠቀም ጀመሩ፡፡ ይህም ለነፃነት ትግላቸው ትልቅ ወኔ ሆናቸው፡፡ ‹‹በፓንአፍሪካኒዝም›› እንቅስቃሴ ውስጥም ኢትዮጵያና ሰንደቅ ዓላማዋ ዋና ምልክትና አንቀሳቃሽ ሞተር ነበሩ፡፡ ይህ ዓለም ሁሉ የሚመሰክረው ሐቅ ነው፡፡ በተለይም በዚያ የቅኝ ግዛት ዘመን በግልጽም ሆነ በስውር ለነፃነት ትግሉ የኢትዮጵያን ዓርማ የማይጠቀም አልነበረም፡፡ ቀስ በቀስ ነፃታቸውን ሲያገኙም በይፋ አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ያለበትን ሰንደቅ ዓላማ በሕግ እያፀደቁ በይፋ ማውለብለብ ጀመሩ፡፡
ለታሪካዊ ማሳያነት ለዓርማቸው ሙሉ በሙሉ አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ቀለማትን ከመረጡ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ጥቂቶቹን እንመለከት፡፡ ከሀገራቱ ስም ፊት ለፊት ይህ ሰንደቅ ዓላማቸው በሕግ ፀድቆ የተውለበለበበትን ዘመን አስቀምጨዋለሁ፡፡ በፎቶም ተመልከቷቸው፡፡ (፡›ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን ዓርማ መጠቀም የጀመሩት ከዐድዋ በበኋላ መሆኑን ለማረጋገጥ የዐድዋ ድል እኤአ በ1896 መሆኑን ልብ ይሏል፡፡)

ጊኒ – እኤአ በ1957
ጋና – 1966
ማሊ – 1961
ሴኔጋል – 1960
ካሜሮን – 1957
ዲ/ሪ/ኮንጎ – 1963
ቤኒን – 1959

እነዚህ ለአብነት የተጠቀሱ ሀገራት (ሌሎችም አሉ) ሙሉ በሙሉ ሦስቱንም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት የተጠቀሙ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ለመለየትም በሚከብድ መልኩ የመመሳሰል ነገር አላቸው፡፡ የቦታ መቀያየርና ኮከብ የማስቀመጥ/ያለማስቀመጥ ብቻ ነው የሚለያያቸው፡፡
በዳሰሳዬ መሠረት አንድም የእኛ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት የሌላቸው ሀገራት ላይቤሪያ (የአሜሪካ በሉት)፣ ሶማሊያ እና ቦትስዋና ናቸው፡፡ (በታሪክ አጋጣሚ ሲጠቀሙ ቆይተው አሁን በተለያየ ምክንያት ቀይረው ይሆን ? ጥናት ይፈልጋል)፡፡ ላይቤሪያ ያው የአሜሪካ የባሪያ መነገጃ ወደብ ስለነበረች ነው መሰለኝ ቁጭ የአሜሪካን የመሰለ ሰንደቅ ዓላማ ነው ያላት፡፡ (ደግሞ ቅኝ ያልተገዛች ተብላ ከእኛ ጋር እኩል ስትጠራ :))
ከእነዚህ ከሦስቱ ሀገራት በቀር ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ቢያንስ አንዱ የእኛ ሰንደቅ ዓላማ ቀለም በሰንደቅ ዓላማቸው ላይ አለ፡፡ ይሄንን በአጋጣሚ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም በቅኝ ግዛት ወቅት ሁሉም በነጮቹ ግፍ ተማረው ነበርና የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የነፃት ምልክት ያላደረገ አንድም የአፍሪካ ሀገር ለማለት ይከብዳልና፡፡

የእኛ ሰንደቅ ዓላማ አይደለም ለእኛ ለመላው አፍሪካም ኩራትና የነፃነት ምልክት ናት፡፡ ቀለሞቿም ከሰማይ ቀስተ ደመና ደማቆቹ ተመርጠው የተወሰዱና ምድራዊ ብቻ ሳይሆን ሰማያዊ ነፃነትንና ጽኑ ቃል ኪዳንንም የሚሰብኩ ናቸው፡፡ ይህ በሃይማኖትና በሌላ አመለካከት የምንከፋፈልበት ምክንያት አይገባኝም፡፡
ይህች ባለ አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ቀለማት ባንዲራችን ዘርና ሃይማኖት የማይገድባት የነፃነት ዓርማ እንጅ ሌላ አይደለችም፡፡ በሃይማኖትና በዘር ቢሆን ኖሮ ለምን መላው አፍሪካ መረጣት ? የእኛን ዓርማ ዓርማቸው ካደረጉ ሀገራት መካከል የእኛን ሃይማኖት የሚከተል የትኛው ነው ? በብሔርስ የሚመስለን አለ ? ይሄ ሁሉ ጣጣ እንግዳ ነገር ነው፡፡ በእውነት ዓርማችንን ዓርማቸው ያደረጉት ሀገራት እነዳይስቁብን በሰንደቅ ዓላማችን ላይ አንድ ዓይነት አቋም ይኑረን፡፡
(በየመንግሥታቱ መሐል ላይ ስለሚለጠፉት ‹‹ልዩ ዓርማዎች›› ምንነትና አግባብነት በሌላ ጽሑፍ እመለስበታለሁ፡፡)

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew