Ethio-Somale

አሳዛኝም፣ አናዳጅም፣ ዘግናኝም፣ አከራካሪ ዜና/መረጃዎች፡-

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮ-ሶማሊ እየተካሄደ ያለውን የቤተ ክርስቲያን ማቃጠልና የሰው ግድያ በጽኑ እንደምታወግዝ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ገልጹ፡፡ ድርጊቱ በአስቸኳይ እንዲቆምም አሳስበዋል፡፡

-›

የኢትዮ-ሶማሌ ተወላጆች ናቸው የተባሉ በርካታ ሰዎች አዲስ አበባ በመከላከያ ሚኒስትር ቢሮ/አምባሳደር አካባቢ ‹በሰልፍ› ተገኝተው በጂግጂጋ እየተካሄደ ያለውን ሁከትና ሥርዓት አልበኝነት መንግሥት ጣልቃ ገብቶ እንዲያስቆምና አብዲ ኢሌን ከሥልጣን እንዲያወርድ ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ፍትሕ ለጅግጅጋ ሕዝብ›› የሚል መፈክር በመያዝም የሰው ግድያና ዘረፋ እንዲቆም አሳስበዋል፡፡ (ጉዳዩን ኢቲቪ ሽፋን እንዲሰጠውም ሕንጻው ድረስ ሄደዋል፡፡)

በጅግጅጋ በሚኖሩ የሌላ ብሔር ተወላጆች (ሐበሾች) ላይ የሚደርሰው ግፍ እጅግ ዘግናኝ ሆኗል፡፡ ሐበሾች የሚላስ-የሚቀመስ የላቸውም፡፡ ሀብትና ንብረታቸው ተዘርፏል፡፡ ምንም የምግብና መጠጥ አቅርቦት ሆነ እርዳታ የለም፡፡ ከከተማዋ መውጣት ሆነ መግባት አይቻልም፡፡ ድረሱልን ቢሉም ደራሽ የለም፡፡ አንዳንድ የከተማው ሰዎች/የስራ ኃላፊዎችም ሐበሽ ተብለው እየተጎዱ ላሉት የቴምር ፍሬ በመኪና ይዘው ለመስጠት ስሞክሩም ሌላ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ ሕዝቡ ቴምር ለመቀበል በመኪናው ዙሪያ ሲሰበሰቡ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች (ልዩ ፖሊሶች ናቸውም ተብሏል) በሕዝቡ ላይ የጥይት ሩምታ በመተኮስ ከአራት ሰዎች በላይ አቁስለዋል፡፡ ሥርዓት አልበኝነቱ እዚህ ደርሷል፡፡
(በኢትዮ-ሶማሌ ክልል የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት ከ8 በላይ ደርሰዋል፡፡ የሞቱ ዜጎች ቁጥርም ከ30 በላይ እንደሚሆን ምንጮች እየተናገሩ ነው፡፡ …እጅግ አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት እርምጃ የማይወስድ ከሆነ የኦሮሚያ፣ የአማራ እና የደቡብ ክልል እንዲሁም የሌሎች ክልሎች ልዩ ኃይል መላክ አለበት፡፡)

-›

በሌላ በኩል ለሦስት ቀናት በድሬዳዋ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮ-ሶማሌ ክልል የሕዝብ ተወካዮች የጋራ የምክክር መድረክ የቆየውና ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።
ተሰብሳቢዎቹ በክልሉ በሰው ህይዎት እንዲሁም በመንግስትና በግለሰቦች ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰና ቤተ ክርስቲያን እየተቃጠለ መሆኑን አውግዘው ድርጊቱ በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል። አሁን ላይ ክልሉን እየመራ ያለው አስተዳደርም ስልጣኑን ለማርዘም ከጎረቤት አካባቢዎች ጋር ሕዝቡን በማጋጨት የአካባቢውን ሰላም ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም በመግለጽም የኢፌዴሪ መንግስትም የክልሉን ሕዝብ ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ በክልሉ የነበረውን ተከባብሮና ተዋዶ የመኖርን ባህል ወደ ብሔር ግጭት በመጠምዘዝ ከሌላ ክልል ተወላጆች ጋር ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላት ተይዘው ለህግ ሊያቀርቡ ይገባል ብለዋል።

እስካሁን በክልሉ ለተከሰተው አለመረጋጋት እና ለሰው ህይወት መጥፋት ዋነኛ ተጠያቂ የክልሉ ባለስልጣናት በመሆናቸው እነርሱን በቁጥጥር ስር በማዋል ሕዝባዊ መሰረት ያለው መንግስት እንዲቋቋምም ጠይቀዋል።

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew