Asab Port

‹‹ አይገርምም ?!? ›› (መላኩ አላምረው)

—›
‹‹ገረመው›› የምለው ሁሉም ነገር የሚገርመው ጓደኛ አለኝ፡፡ እርሱ የማይገረምበትን ነገር ፈልጎ ከማግኘት ከጅቦች መሐል ውሻ ወይም ከተኩላዎች መሐል በግ ማግኘት ይቀላል፡፡ በቃ ሁሉም ነገር ይገርመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ስም፣ የጣና ውኃነት፣ የመለስ መሞት፣ የአክሱም ሐውልት ከድንጋይ መሆኑ፣ ላሊበላ ከአለት መፈልፈሉ፣ የፍልፍሉ ጥርስ መሸረፍ፣ የኃይሌ ገብረ ሥላሴ መሮጥ፣ የየኃይለማርም ቁመት…. በቃ ሁሉም ይገርመዋል፡፡ ልክ እንዳገኛችሁ ‹‹አይገርምም ግን…›› ይላችኋል፡፡ ‹‹ምኑ›› ስትሉት… ‹‹የአንተ እክሌ መባል›› ሊላችሁ ይችላል፡፡ በስማችሁ ተገርሞ ሊያስገርማሁ እኮ ነው፡፡
—›
እየተዛዘን እንጅ ጎበዝ… አሁንም ከትናንቱ የጠሚዶር ዐቢይ ንግግር ላይ ናችሁ? ትናንት ስናማቸው አምሽተን ስናማቸው ያደርን ‹‹አሸባሪዎች›› ዛሬም እነርሱን ስንቦጭቅ ውለን እንደር እንዴ? ኧረ ሼም ምናምን የሚባል ነገር አለ እኮ፡፡ (ኤርትራ ኢትዮጵያን መውረሯ ሼም ነው… አሉ የቦሌ ልጆች የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ለማውገዝ ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ ጊዜ፡፡ የሰሞኑን ሰልፍ የምናፍቅበት ምክንያት የቦሌን ልጆች መፎክር ለማየት መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ ይፈቀድልኝ፡፡ ያው የሰልፍ አድናቂ ባልሆንም ለአንዳንድ ገራሚና አስገራሚ መፎክሮች ሲባል ግን ሁሌም ሰልፍ ቢኖር እላለሁ፡፡ ለምሳሌ ቀጣዩ የሸገር ሰልፍ ብምን አይነት ምስል እንደሚሞላ አስቡትማ…. በኦነግ ባንዲራ፣ በአኖሌ ሐውልት ይፍረስ ሥዕል፣ በቀን ጅቦች ምስል…. ብቻ የሰልፉ ጥቅምም ሆነ ጉዳት ለይቶ ባይዘልቀኝም…. እስኪደርስ ግን ቸኩያለሁ፡፡ የዓመት መዝናኛ ለመሸመት፡) ከቦሌ ልጆች ሐሳብ ሳንርቅ…. የቦሌ የፎቅ ጫካ ግን አይገርምም? የማነው ግን?)
—›
ወደ ገረመው መገረም እንመለስ፡፡ ገረመው የትናንቷን የኃማደን ሽሙጤን አንብቦ ደወለልኝ፡፡
‹‹እኔ እምልህ… ኃይለማርያም ግን አይገርምም?››
‹‹ምኑ ነው የሚገርመው?››
‹‹ሥልጣን መልቀቁ ነዋ!››
‹‹በለው… ያንተ ነገር ባመቱ ይገርምህ ጀመረ፡፡ ቆይ ወዶ ነው እንዴ የለቀቀው… ለምን ይገርምሃል? ለእኔ ከእርሱ መልቀቅ አለመልቀቁ ነበር የሚገርመኝ!›› አልሁት፡፡ ትንሽ ዝም አለና ቀጠለ፡፡
‹‹አሃ… ልክ ነህ መለኛው፡፡ እንዲያውም ከእርሱ ይልቅ የጀኔራል ሳሞራ መልቀቅ ነው የሚገርመው››
‹‹ውይ… አንተ ደግሞ የማይገርምህ የለም፡፡ ጥሮታ ወጣ እንጅ በፈቃዱ አልለቀቀ፡፡ ዕድሜውን በታንክ ገድቦ አያቆመው… ይሄ ምኑ ይገርማል? በእናትህ ወሬ ቀይር…››
—›
ይልቅ የሚገርም ነገር እናውራ፡፡ ቆይ ግን የኢህአዴጎች ‹‹አሸባሪዎች›› መባል አልገረማችሁም? የምር ስድብ እኮ ነው፡፡ መንግሥትን ያህል ነገር… በአደባባይ… ያውም በፓርላማ አሸባሪ!!!! ማለት የምር ይገርማል፡፡ ስለዚህ ንግግሩ ብቻ እንኳን መሰለፍ ለምን አንሮጥለትም ግን? የእኛ ሕዝብ ግን አይገርምም? ራሱ ሲፈራው የኖረን ስድብ እየሰደበለትም አይረካም፡፡ በስድብ መርካት ግን ምንድነው? ምንነቱን የማታውቁትን ነገር ስትናገሩ ግን አይገርማችሁም? እኔማ ዝም ብሎ ነገር ይገርመኛል፡፡ ዝም ብሎ ድጋፍ፣ ዝም ብሎም ተቃውሞ ይገርመኛል፡፡ ዝም ብሎ መውደድ ዝም ብሎም መጥላት ይገርመኛል፡፡ ኧረ አመዛዛኝ አእምሮ ሆይ ወዴት አለሽ? በሀገሬ ምድር ምክንያታዊ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ መቼ ይሆን የምናየው?
በነገራችን ላይ ስብ ብርቅ አይደለም፡፡ ብርቅ አይደለም ማለት ግን አይገባም ማለት አይደለም፡፡ ይገባል እንጅ!!! ለምሳሌ… ዐቢይ ‹አሸባሪዎች›… ያላቸውን… ልቡ አይደንግጥና መንጌም ‹‹ወንበዴዎች›› ይላቸው ነበር። ስልጣን እንደያዙ ጀምሮ ያንን የስድብ ብድር ሊመልሱ እነርሱም መንጌን ‹‹ሰወ በላ፣ ቡቸር… ምናምን›› አሉት። እስኪለቅ ሰደባቸው… እስኪበቃቸው ሰደቡት፡፡
በስድብ መስፈርት ግን ከሁለቱ ማን ነበር ትክክለኛ ስድብ የተሳደበው?
(ሀ) ጓድ ሊቀመንበር (ለ) ጓድ መንግስቱ (ሐ) እነርሱ (መ) ሀ እና ለ (ሠ) ሁሉም፡፡
—›
ገረመው ቅድም ደወለ፡፡ ‹‹ሚካኤል እና የእኔ ስም አወጣጥ ታሪካዊ ግጥጥሞሽ›› የሚለውን ግጥሜን አንብቦ መገረሙን ሊነግረኝ ነው መደወሉ፡፡
‹‹አባትህ ግን አይገርሙም?›› አለኝ።
‹‹እንዴት?›› አልሁት።
‹‹አንተን መልአኩ ማለታቸው። ስምህና ግብርህ እኮ አንድ ናቸው። መልክህም ቢሆን መልአክ ነው የምትመስለው…›› እንደዚህ አይነቱማ መገረም ሳይሆን ጅንጀና ነው… አልሁና… ‹‹ገሬ… ከእኔ ምን ፈልገህ ነው የደወልህ?›› አልሁት።
‹‹አይ መሌ ያራዳ ልጅ … ይች አራዳነትሽ እኮ ናት የምትገርመኝ፡፡ ያው…. የቤት ኪራይ ደርሶብኝ እስከደመወዝ….›› መቼ አጥቸው፡፡ ይህችን ዓይነት ጅንጀና መሰል መገረም የሚነግረኝ ለሱሱ ብር እስክሰጠው ነው። ደግሞ ማመካኛው አይገርምም? ለሱስ ብር ላለማለት ‹ለቤት ኪራይ› …..ከእናት አባቱ ጋር እኮ ነው የሚኖረው፡፡ ሱስ ግን አይገርምም? ለምሳሌ የሀገር ፍቅር ሱስ! ስድብ ሱስ! የሌብነት ሱስ! የጅብነት ሱስ! (ውይ ይች ጅብነት ደግሞ ከአፌ ገብታ አልወጣ አለች እኮ… ሰሞኑን ግን ጅቦች ደንግጠው ሞቱ መቼም፡፡ አጥንቱም ሥጋ ‹ስቅ!› እያላቸው አይታዩአችሁም? …ሃሃሃ… የጅብ ተፈጥሮ ግን አይገርምም? ሆዳም ነገር እኮ ነው፡፡ ደግሞ የጥርሱ ስላት… የአፉ ስፋት… ፡)
አይ ገረመው ግን…. አሁን ጅብ እያለ የእኔ ስም ይገርመዋል? ባይሆን ደስ ይላል፡፡ የመልአክ ስም ደስ ይላል። ግን ሸክም ነው። እንደ ስም ካልኖሩ ያሳፍራል። ለስምማ ‹‹ነፃ አውጭ›› የሚል ስም ያልያዘ የትግል ግንባር አለ እንዴ? ሁሉም ግን ‹‹ነፃነትን ገፋፊ›› ናቸው፡፡ ስም ብቻ!!! ‹‹ሁሉም ነፃ አውጭ ነኝ ባይ… በተግባር ግን ወንበዴ!›› አለ መንጌ ዘዝመርባብዌ። ፡)
—›
ይልቅ ሌላ አስገራሚ… ነገር! የአሰብ ነገር ግን… አልገረማችሁም? ‹‹አሰብን ስንሰጥ ተወያይተን ነበር እንዴ?›› የምትለዋ ንግግር ያለገረመችው ካለ በምንም አይገረምም። ለካንስ አሰብ የእኛ ነበረች፡፡ ይኸው ሳንወያይ እንኳን ሰጡብን፡፡ ይገርማል፡፡ ዐቢይሻም ግን እዚች ላይ ገራሚ ነገር ተናገረ፡፡ አሰብን ሳንወያይ ስለሰጠን ባድመንም ወልቃይትንም ሳንወያይና ሳንስማማ እንስጥ እንዴ? ‹‹የማይሆነውን›› አለ አማራ !!! አማራ ግን አይገርምም? እስካሁን በብአዴን መመራቱ፡፡ ብአዴንስ አይገርምም? አማራን ለ27 ዓመት መራሁህ ማለቱ፡፡ ወዴት ነበር ግን የመራው? በጣም የሚገርመው እኮ ይህ ነው፡፡ ወዴት እንደመራው አለማወቁ፡፡ አይ ብአዴን… ይገርማል፡፡

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew