እንኑር ካላችሁ እንደ ‹‹ደሴ›› እንኑር !

‹‹የገራዶ ሜዳ ለምን ‘ገራዶ’ ተባለ ?›› መልሱን ‹‹የሆነ… የተጋረደ ቦታ ስለሆን… ከደሴ የአብዛኛው ሰፈር እይታ ስለተጋረደ.. ወዘተረፈ” ካላችሁ… ተሳስታችኋል ወይም መልሱ ሙሉ አይደለም። በስንትና ስንት እልህ አስጨራሽ ጥናት የደረስሁበትን የገራዶ ትንቢታዊ ትርጉም ልንገራችሁ… ገራዶ “ገራዶ” የተባለበት ምሥጢር በዋናነት ፍቅርን ከመናገሻችን ከ4 ኪሎ ጋርዶ ደሴ ላይ ስላስቀመጠ ነው። ካላመናችሁኝ ወላ “በጂኦግራፈር” የአቅጣጫ ጠቋሚ ወላ በናሳ የሳተላይት ምስል አረጋግጡ። ጥንት ለገራዶ ስያሜ የሰጡት ደግሞ ነቢያት መሆን አለባቸው። (፡እንዲያውም ይህን ትንቢታዊ ስያሜ የሰጠው ትንቢቶቹ ሁሉ “ደረቅ ወንጌል” በመባል የሚታወቁለት ኢሣይያስ ሳይሆን አይቀርም። እርሱ ተነበየ ማለት በቃ በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥታ ይፈጸማል-ተፈጽሟልም።) የገራዶ ትንቢታዊ ስያሜም ይኸው አሁን እየተፈጸመ ነው። እንዴት ? ተከተለኝ። አጉል “የአዋቂ ነኝ” ትምክህትህን አራግፍና ልብህን ለፍቅር አዕምሮህን ለአዲስ እውቀት፣ ዓይኖችህንም ለአዳዲስ እይታዎች ከፍተህ ተከተለኝ። የሚሰማኝ አጥቼ እንጅ… እኔ እኮ ገና ድሮ ደሴን እንዳየኋት ነበር… . ፍቅርን ከሀገሬ ምን መንፈስ ወሰደው ? ሳስበው ፥ ሳስበው… ደሴ ላይ ከትሞ – ገራዶ ጋረደው !!! . የምትል ስንኝ ቋጥሬና ከማመልከቻ ጋር አያይዤ ‹‹እባካችሁ የሕግና ሥርዓት ምንጭና መዳረሻ የሆነው የሀገራችን መናገሻ መዲና በተለይም የቤተ መንግሥቱ የአቀማመጥ አቅጣጫ ከገራዶ ሜዳ አንጻር ትይዩ ይሁን። ፍቅርን ከምንጩ (ከደሴ) ሰብስቦና ጋርዶ የያዘውን ቦታ ከመዲናችን በቀጥታ ማየት ካልቻልን ይከብዳል። ከፍቅር ተጋርዶ መብላትም ሆነ መጠጣት ቁንጣንና ስካር እየሆነ ትዕቢትን ይወልዳል። ትዕቢትም ንቀትን፣ ንቀትም ጥላቻን፣ ጥላቻም ዘረኝነትን፣ ዘረኝነትም መከፋፈልን፣ መከፋፈልም መለያየትንና መበታተንን ያመጣል… ይህኔ እንወቅበት። የገራዶ ነገር ይመከርበት። የመናገሻችንን አቅጣጫ መቀየር ካልቻልን የራሱን የገራዶን ወይም በዙሪያው ያሉ ተራሮችን አቅጣጫ እንቀይረው (ሰው ሠራሹን የቅራቅንቦ ግንብ ከማፍረስ ምትክ የሌላቸውን የተፈጥሮን ውብ ሕንፃዎች ማፍረስ እየቀለለን ስለሆነ)… ከገራዶ ወደ መናገሻችን አቅጣጫ ያሉ ተራራዎች በሙሉ ተንደው ይጥፉልን ! ይታሰብበት… ይመከርበት!›› ብዬ ነበር። ማን ይስማኝ ??? . ለማንኛውም ሰሚ አጣሁ ብዬ ቁጭ አልልም። ሄጃለሁ ! ፍቅርን ያላችሁ ተከተሉኝ። በምዕናባዊ ተረት ላደነዝዛችሁ ሳይሆን ተግባራዊና ሕያው ፍቅርን ላወጋላችሁ ሄጃለሁ። ‹‹ወዴት ?›› ከሀገር መዲና ወደ ፍቅር መዲና… ከሸገር ወደ ወሎ-ደሴ ዘልቄያለሁ ! ለኑሮም ባይሆን ትንሽ ሰነባብቶ… ገራዶ የጋረደውን ፍቅር ኮርጆ/ቀድቶ ለመመለስ ሄጃለሁ። አዎ ፍቅርን ከደሴ ኮርጄ ‹‹ፈተናዬን›› ላልፍበት… ሄ ጃ ለ ሁ !!! ‹‹ደግሞ ፍቅር ይኮረጃል እንዴ ?›› ካላችሁ… ‹‹ቀላል ይኮረጃል እንዴ ! ታዲያ ይህን የፍቅር እጦት ፈተና በምን ያልፉታል ? በዚህ ዘመን ፥ የሰው ልጅ ልብ ፍቅርን ይዞ መኖር ሲያቅተውና አንደበቱ ጥላቻ ጥላቻ ሲያቀረሽ ፥ አፍንጫው ባሩድ ባሩድ ሲያሸት ፥ ጆሮው የሽብርና የጦርነት ፣ የመከፋፈልና የዘረኝነት ወሬ ብቻ ሲሰማ ፣ ዓይኖቹ ደም ሲለብሱና ውስጠቱ በቀልን ተመልቶ ምድሩን በደም ሊያጨቀያት መንገዱን ሲጠርግ እያየን… ፍቅርን እንደ ደሴ ካሉ የፍቅር አድባራት ኮረጅ ! ኮረጅ ! አድርገን ለሌሎችም በፍጥነት ካላከፋፈልን እንዴት እንኑር ??? ስንት ነገር እየተኮረጀላት በምትኖር ሀገር ምነው ፍቅርን መኮረጅ ጥያቄ አስነሳ ???›› መልሴ ነው። እውነቴን ነው የምላችሁ ጎበዝ… ከፊት ለፊታችን ትልቅ ፈተና አለ። ማለፊያው ደግሞ ፍቅርና ፍቅር ብቻ ነው። ይልቅ ዝም ብለህ ‹‹የፍቅር ተምሳሌት ነን›› እያልህ በባዶ ልብህ ከመኮፈስ… እንጥፍጣፊም ቢሆን ፍቅር ያለህ አጥብቀህ ያዝ ! የሌለህ ካለው ኮርጅ ! ኧረ የሚኮረጅም ሳይጠፋ ፍጠን ! . በዚህ ሰዓት ለሀገራችን የሚያስፈልጓት ሀገራቸው ከውጭ የኮረጀችውን ሳይንስ አጥንተው ካልሆነም እንደገና ኮርጀው የሚያልፉ ‹‹ሀገር ተረካቢ›› ወጣቶች አይደለም። ጥሩ የፍቅር ኮራጆችና አስኮራጆች ግን በጽኑ ያሻሉ። (ት/ሚኒስትር ግን ‹‹ፈተና መኮረጅ ውርደት ነው›› ሲል ራሱን የትምህርት ፖሊሲውን እስከ ሥርዓተ ነጥቡ ከውጭ የኮረጀው መሆኑ ትዝ አይለውም? ‹ጥሎብን የኮረጅነውን እንኳን ሲኮርጁብን አንወድም›።) ‹‹ፍቅር በገንዘብ አይሸጥም›› እንጅ ‹‹በስሜት ሕዋሳት አይኮረጅም›› ያለው ማነው? ይልቅ የምንኮርጀውም ጨርሰን ሳናጣ ተግተን እንኮርጅ። ፍቅር ካለ ቁሳቁስ ‹‹በእራት ላይ ዳረጎት›› ሆኖ ይመጣል። ‹‹በመጀመሪያ ፍቅርን እሹ… ቁሳቁስ ሁሉ ይጨመርላችኋል›› – ወቅታዊ ጥቅስ ነው ጻፈው። … ወድጄ ፣ ጊዜ ኖሮኝ ፣ ተመችቶኝም ለመዝናናት አይደለም በዚህ የወከባ ዘመን ሥራዬን ጥዬ ወደ ወሎ-ደሴ መሄዴ። ፍቅር ቢጠራኝ ነው። *ፍቅር ያዋለደው እምነት ያዋሐደው ሕዝብ እርስ በርሱ ሲነካከስ ሳይ… ፍቅርን ከግርዶሽ ለማውጣት ልቤ ሂድ ሂድ ቢለኝ ነው። መልካም መታደላችንን ሳጠቀምበት መጥፎ አዳዲስና እንግዳ ልማዶቻችን እንዳያጠፉን መነቃቂያ ቃጭል ለማቃጨል ነው። ደወሉን ለሚደውሉት መንገድ ለመጥረግ ነው መሄዴ………. ወደ ወሎ-ደሴ ! ‹‹ኢትዮጵያ የፍቅርና የመቻቻል ተምሳሌት ናት›› የሚለውን አባባል ‹‹ፍጹም ቅጥፈት ነው ፣ ውሸት ነው›› እንዳልል ከሚያደርጉኝ አካባቢዎች አንዱ ወሎ ነውና- ደሴ ! በኢትዮጵያ ‹‹መቻቻል አለ›› እውነት ነው! ‹‹ሀገራችን ፍቅር በፍቅር ናት›› ካልን ግን ቅጥፈት ነው። መቻቻልንና ፍቅርን ለዩ፡፡ መቻቻልም… ወደህ ትችላህ!!! ለመኖር የማይቻል የለም፡፡ በመቻቻል የሚኖር ሁሉ የማይቻል ሲመጣ መቆጣቱ አይቀርም፡፡ መቻቻል ገደብ አለው፡፡ ፍቅር ግን ገደብ የለውም፡፡ በፍቅር የሚኖር ሁሉን ስለፍቅር ይተዋል፡፡ በሀገራችን…… ፍቅር እስከሙሉ ግርማ ሞገሱ ቁጭ!!!! ያለው ደሴ ላይ ነው። (፡ግርማ ሞገሱን ሊያሳጡት ከግራም ከቀኝም እየጎነታተሉት ነው የሚባል ሀሜት አለ። አትስሙት። የተነቃነቀ ሁሉ አይወድቅም፣ ነፋስ አቧራን እንጅ አለትን አያነሳም በሉት። የወሎ ፍቅር በጽኑ የአለት መሠረት ላይ እንጅ በአሸዋ ላይ አልታነጸምና አትስጋ በሉት። ባይሆን ይህን ጽኑ ፍቅር እየኮረጅህና እያባዛህ ለሁሉም አዳርስ እንጅ ዝም ብለህ አታሟርት በሉት። እንዲህ ልክ ልኩን ንገሩት… የታባቱ ! ሟርተኛ ! ይልቅ ፍቅርን ከየቤተ እምነቱ መሪዎች አጥታችሁት ተስፋ ከመቁረጣችሁ በፊት ደሴ ኑማ። ) . እንኑር ካላችሁ እንደ ደሴ እንኑር ልዩነት ሳይለየን ፍቅርን እንዘምር ! . ለደሴ የሚመጥነው ብቸኛ ቃል ፍቅር ነው። ሰብዓዊ ፍቅርርርር ! ወሎ ደሴ ሄደህ ምን አጥተህ ! ፍቅር ካለ ምን ጎድሎ ! . ‹‹ወሎ ደሴ መጀን ፍቅር ነው ያበጀን !›› . መልካም ውሎና አዳር ያድርግልንማ ! ደሴ ላይ ከትመን ፍቅርን እናወጋለን። ቢያሻን በደሴ ንጹህ ውሃ ቢያሻን በመድኃኔዓለም ሰፈሩ የእነ እማማ ዜማነሽ ጠላ እያወራረድን…. በሰላሙ ያኑረን ! እንደ ሰው ያክብረን ! እንደ ደሴ ያፋቅረን !

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew

Leave a Reply

Your email address will not be published.