Mohamed Ali

ኧረ ማነህ? አገርህ ወዴት ነው? ኤዲያ! ማንነትማ “ዱሮ ቀረ” / መሐመድ አሊ መሐመድ

አይ ዱሮ፣ ዱሮማ ድንጋም ዳቦ ነበር ይባላል። ይኸንኳ ተረት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ግን የዱሮው ዘመን ስንት ነገር ይዞ አልፏልኮ፡፡ ሌላውን እንተወውና; ዱሮኮ ከወዴት መሆንህ እንጅ ማንነትህ? ግድ አይሰጥም ነበር፡፡ ዛሬማ ወዳጄ; ጨዋታው ወደገደለው ነው፡፡ ስለማንነትህ እቅጩን ሳትናገር ዙሪያ ጥምጥም ብትሄድ ማንም አይሰማህም ወይም አያምንህም፡፡ ለመሆኑ የማንነት መገለጫ ምን ይሆን?

የማንነት መገለጫዎች ብዙ ናቸው፡፡ በቀላሉ የቀበሌ መታወቂያ ስናወጣ ቤተሰባዊ ማንነታችንን (ሥም አስከ አያት)፣ ፆታዊ ማንነታችንን፣ የዕድሜ ክልላችንን/መደባችንን፣ አካባቢያዊ ማንነታችንን (የትውልድ ቦታ)፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መሠረታችንን (ሥራ/ሙያ) እንጠየቃለን፡፡ ለዘመነ ወያኔ ምስጋና ይግባውና የብሔርና የሃይማኖት ማንነት ካልታከሉበት ማንነት ጎደሎ ነው፡፡

ቀደም ባለው ቢሆን የአንድ ሰው ማንነት ዋነኛ መለያና መታወቂያ ቤበተሰባዊ ማንነቱ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ “የእከሌ አበሉ ልጅ”፣ “የእነከሌ ቤተሰብ” ነው መባል የተለመደና የሚያኮራም ነበር፡፡ በዚያ በደጉ ዘመን በተለይ በተርታው ማህበረሰብ ዘንድ ብሔር ወይም ሃይማኖት ብዙም ግድ አይሰጥም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የየትኛውም ብሔር አባል ይሁን፣ የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ቢሆን አንድ ሰው መታወቅና መኩራት የሚፈልገው በቤተሰባዊ ማንነቱ ነበር፡፡ እርግጥ ነው ቤተሰባዊ ማንነት የመደብ ልዩነት መነሻና አመላካች ሊሆንም ይችላል፡፡ ይሁን እንጅ ቤተሰባዊ ማንነት የመደብ ልዩነትን ከማመልከት ባለፈ ለህዝብ መከፋፈልና ለሀገር ደህንነት ሥጋት ሊሆን የሚችልበት ዕድል አልነበረም/ሆኖም አያውቅም፡፡

በሀገራችን ከቤተሰባዊ ማንነት ቀጥሎ የሰው መታወቂያው አካባቢያዊ ማንነቱ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የዛሬን አያድርገውና የሐረር ልጅ ነኝ፣ የጎንድር ልጅ ነኝ፣ የጅማ ልጅ ነኝ፣ የደሴ ልጅ ነኝ፣ የናዝሬት ልጅ ነኝ፣ የአስመራ ልጅ ነኝ፣ የአምቦ ልጅ ነኝ፣ የመቀሌ ልጅ ኝ፣ የአሰብ ልጅ ነኝ፣ የአይሣኢታ ልጅ ነኝ፣ የአዋሳ ልጅ ነኝ፣ የወልዲያ ልጅ ነኝ፣ የአርባምንጭ ልጅ ነኝ፣ የአሶሳ ልጅ ነኝ፣ የድሬ ልጅ ነኝ፣ የአሰላ ልጅ ነኝ፣ የጂጂጋ ልጅ ነኝ፣ የደብረብርሃን ልጅ ነኝ … ወዘተ ማለት በቂ የማንነት ማሳያና የኩራት ምንጭም ነበር፡፡ ማንም ሰው ቢሆን ከየት መሆኑን እንጅ የብሔርና የሃይማኖት ማንነቱ ብዙም ትኩረት አይሰጠውም ነበር፡፡ ጭራሽ የማይተዋወቁና በዕድሜም የሚራራቁ የአንድ አካባቢ ሰዎች ሌላ ቦታ ድንገት ቢገኛኙና የአንድ አካባቢ ሰዎች መሆናቸውን ቢያውቁ/ቢተዋወቁ የአንዱ ልብ ለሌላኛው በቀላሉ የሚከፈትበት፣ ብሎም በመካከላቸው ፍቅርና መተማመን የሚፈጠርበት ዕድል ሰፊ ነበር፡፡ በዚህ መልኩ አካባቢያዊ ማንነት የአንድን አካባቢ ሰዎች እርስ በርስ ከማስተሳሰር ባለፈ በሌሎችና በሀገር አንድነት ላይ ሥጋት የሚፈጥር ሆኖ አያውቅም ነበር፡፡

ከአካባቢያዊ ማንነት ባለፈ ሌሎችንም ሊያስተሳስሩ የሚችሉ ሌሎች የማንነት መገለጫ ማዕቀፎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተለይ የበደርግ ሥርዓትን ተከትለው የመጡት “የመላው ኢትዮጵያ ወጣቶች ማህበር” (አኢወማ)፣ “የመላው ኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር” (አኢሴማ) የሚሉ አደረጃጀቶች የፆታ ማንነትና የዕድሜ ገደብ/መደብ መገለጫዎች ሆነው ያገለግሉ ነበር፡፡ እነዚህ የማንነት መገለጫዎችም ቢሆኑ ተመሳሳይ ጾታ ያላቸውንና በተመሳሳይ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያስተሳስሩና አንድነታቸውን የሚያጠናክሩ እንጅ ህዝብን ለመከፋፈልና የአገርን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ በነዚህ የማንነት መገለጫ ማዕቀፎች ውስጥ ለመግባት የብሔርም ሆነ የሃይማኖት መመዘኛዎች ሳያስፈልጉ በፆታ ሴት፤ እንዲሁም በዕድሜ ወጣት ሆኖ መገኘት ብቻ በቂ ነበር፡፡ ስለሆነም ስለሆነም የዚህ ዓይነቶቹ የማንነት መገለጫ ማዕቀፎች ሌሎች የማንነት መገለጫዎችን አቅፈው የመያዝና በሂደት የጋራ ዓላማና እሴቶችን ለማሳደግ የሚረዱ ነበሩ/ናቸውም፡፡

ከዚህም ሌላ፣ ሌሎችም የአንድን ሰው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መሠረት ሊያሳዩ የሚችሉ የማንነት መገለጫዎችንም መጥቀስና በዝርዝር ማዬት ይቻላል፡፡ ከብዙ በጥቂቱ፣ “የገበሬዎች ማህበር”፣ “የሠራተኞች ማህበር”፣ “የመምህራን ማህበር”፣ “የነጋዴዎች ም/ቤት”፣ “የአካል ጉዳተኞች ማህበር” … ወዘተ የመሳሰሉ የማንነት መገለጫዎች የጋራ አጀንዳና ዓላማን ለመቅረፅ የሚያግዙና አንድነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ራሱን እኔ “ገበሬ” ወይም “ሠርቶ አደር” ወይም “መምህር” ወይም “ነጋዴ” ወይም “አካል ጉዳተኛ” ብሎ ማንነቱ የሚገልፅበት ሁኔታ መኖሩ እሙን ነው፡፡ እነዚህና መሰል የማንነት መገለጫዎች ማዕከል የሚያደርጉት የጋራ ጥቅምንና መብትን እንጅ የብሔር ወይም የሃይማኖት ማንነትን አልነበረም/አይደለምም፡፡ ስለሆነም እነዚህ የማንነት መገለጫዎች የሃይማኖት ልዩነትና የብሔር አጥር ሳይከልላቸው ህዝብን/የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን በዓላማና በጋራ ጥቅም የማስተሳሰርና ሀገራዊ አንድነትን የማጠናከር ፋይዳ ነበራቸው፤ አሁንም ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ይሁንና አለመታደል ሆኖ፣ ወያኔ/ኢህአዴግ ወደሥልጣን ሲመጣ ህዝብን ለመከፋፈል ከተጠቀመባቸው ስልቶች አንዱ፣ ከብሔርና ከሃይማኖት አጥር በዘለለ ህዝብን በማስተሳሰር ረገድ ትልቅ አገራዊ ፋይዳ የነበራቸው የሙያ ማህበራትና “የማንነት መገለጫዎች” የነበራቸውን ተቋማዊ ነፃነትና አቅም ማዳከም/ማሳጣት ነበር፡፡

እነዚህን በሀገር ደረጃ የማንነት መገለጫ ሊሆኑ የሚችሉ መዋቅሮችና እሴቶችን በማዳከም በምትኩ የብሔርና የሃይማኖት ማንነቶችና እሴቶች ከሌላው ይበልጥ ጎልተው እንዲታዩ ተደርጓል፡፡ ለመሆኑ የብሔርና ሃይማኖታዊ ማንነቶችስ ቢሆኑ ህዝብን ከመከፋፈል በተቃራኒ በራሳቸው ትስስርን ሊፈጥሩና አንድነትን ሊያጠናክሩ የሚችሉባቸው አግባቦችና ዕድሎች የሉም ወይ? በሌላ አነጋገር፣ አንዱ ሊፈጥረው የሚችለውን ስንጥቅ/ቀዳዳ፣ ሌላው መርፌና ክር ሆኖ ለመስፋት ወይም ስሚንቶ ሆኖ ለማጣበቅ አይረዳም ወይ? እስቲ ለመነሻ ሃይማኖታዊ ማንነትን ወስደን እንመልከት?

የኦርቶዶክስ፣ የእስልምና፣ የፕሮቴስታንት፣ የካቶሊክ፣ የጆሆባ፣ የባሃኢና የሌሎችም እምነቶች ተከታዮች የአንድ ብሔር አባላት ብቻ እንዳልሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሃይማኖቶች የየራሳቸው እሴቶችና፣ የእያንዳንዱን እምነት ተከታዮች የማስተሳሰር ኃይል ብቃት ያላቸው ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው፣ ሃይማኖታዊ እሴቶቹ ከሰማያዊ ተልዕኮና ከእያንዳንዱ አማኝ “ነፍስ” ወይም መንፈሳዊ ህይወት ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ስለሆነ ከየትኛውም ምድራዊ ዓላማና ሥጋዊ ፍላጎት በላጭና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ለምሣሌ ከጥቂት ዓመታት በፊት “የእምነት ነፃነታችን ተጥሷል” የሚል መነሻ የነበረው የሙስሊሞች ተቃዉሞ የብሔርም ሆነ የሌሎች ማንነቶች አጥር የሚከልለው አልነበረም፡፡ ከዚያ ልምድ መገንዘብ የሚቻለው፣ ሃይማኖታዊ ማንነቶችና የጋራ እሴቶቻቸውን ለገንቢ ዓላማ ከተጠቀምንባቸው ወደ ጥፋት ሊወስዱን/ሊያመሩን የሚችሉ ጽንፈኛ የብሔር አስተሳሰቦችን ለመግራትና ከዚህ አንፃር ተለጥጠው የሚታዩ ግንጥል ማንነቶችን ለማረቅ ይረዳሉ፡፡

ይሁንና የሃይማኖት ማንነቶችም በወግና በሥርዓት ካልተያዙ በራሳቸው ሌላ የመከፋፈል አደጋን ሊፈጥሩና ወደባሰ ጥፋት ሊያመሩ የሚችሉባቸው ዕድሎችም አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የብሔር ማንነቶች ተመልሰው ገንቢ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩም ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እንዴት? በሉኝማ! የሃይማኖት ማንነትና ልዩነትን መነሻ አድርገው የተለያዩ ጽንፎችን የያዙ ሰዎች ከሃይማኖታዊ ማንነታቸው በመለስ፣ የአንድ ብሔር አባላት መሆናቸው በሌላ መንገድ ሊያስተሳስራቸው ይችላል ለማለት ነው፡፡ ምክንያቱም የአንድ ብሔር አባላት የሃይማኖት ልዩነቶቻቸው እንደተጠበቁ ሆነው እርስ በርስ የሚያስተሳስሯቸው የራሳቸው የጋራ እሴቶች እንደሚኖሯቸው እሙን ነው፡፡ ስለሆነም የብሔር ማንነትን በሌላ ማንነት ሳቢያ ሊፈጠር የሚችልን መከፋፈል ለመግታት ልንጠቀምበት እንችላለን ማለት ነው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንድ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ቢኖር፣ የሃይማኖትም ሆነ የብሔር ማንነቶችና የጋራ እሴቶች፣ ልዩነቶችንና ግጭቶችን የመፍታት/የመግታት ዋስትና ሊሰጡ አይችሉም፡፡ ለዚህ እንደትልቅ ማሳያ ሊወሰድ የሚችለው የጎረቤት ሶማሊያ ጉዳይ ነው፡፡ የሶማሊያ ህዝብ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ብሔር፣ አንድ ቋንቋና፣ እነዚህ የሚፈጥሯቸው የጋራ እሴቶች ያሉትና አንድ ወጥ ማንነት አለው ሊባል የሚችል ነው፡፡ ይሁን እንጅ፣ አንድ ከሚያደርጉን ጉዳዮች ይልቅ ለልዩነቶቻችን የበለጠ ትኩረት/ቦታ ከሰጠን የልዩነት አድማስና የመከፋፈል አደጋ ማቆሚያና ጥግ እንደሌለው የሶማሊያ ሁኔታ ጥሩ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

በነገራችን ላይ ሌሎች የማንነት መገለጫዎችም ቢሆኑ በወግና በሥርዓት ካልተያዙ ወደ ጥፋት ሊያመሩ እንደሚችሉ በርካታ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሩቅ ሳንሄድ በተለይ በወጣቶች ተፅዕኖ ሥር የወደቀው የ1966ቱ አብዮት በሀገራዊ እሴቶችና ዘላቂ ጥቅሞች ላይ ያስከተለውን ውድመትና አጠቃላይ ውድቀት ወስደን መተንተን እንችላለን፡፡ ዛሬም ቢሆን “ያ ትውልድ” – “ይህ ትውልድ” እየተባባሉ አንዱ ወደሌላው ጣቱን ሲቀስር መታዘብና ሌላ አደጋን ማሽተት ይቻላል፡፡ ከዚህም በመነሳት እያንዳንዱን የማንነት መገለጫ ከሚገባው በላይ ለጥጠንና ልዩነትን ሊያጎላ በሚችል መልኩ ከመጠቀም ይልቅ፤ ከእያንዳንዱ የማንነት መገለጫ ትስስሮቻችንን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ሰበዞችን በመምዘዝ፣ አንድነታችንን አጥብቀን መስፋትና ማስጌጥ እንደምንችል አስረግጦ መናገር ይቻላል፡፡

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew