ከጓድ መንግሥቱ ለዶ/ር ዐቢይ የተጻፈ ደብዳቤ

ከጓድ መንግሥቱ ለዶ/ር ዐቢይ የተጻፈ ደብዳቤ
(መላኩ አላምረው)
—//—
“እኔ ምልህ ዐቢይ…
ከእኔ መውጣት ኋላ የታሰረን ሁሉ፤
ይቅር ይቅር እያለህ ትፈታለህ አሉ።
.
በሲአይኤ ሴራ፣ በተሰራብኝ ሸፍጥ፣ የተሰደድሁ እኔ፤
ላገሬ እንዳልበቃ፣ ሞት የፈረደብኝ፣ ሙትቻ ወያኔ…!
.
አሁን ባንተ ዘመን፣ አገሬ ካልገባሁ፣ መቼ ልገባ ነው?
አይ የልጅ ነገር፣ እረሳኸኝ እንዴ? ዝም አልከኝ ምነው?

ሲያነደኝ የኖረ – የባንዲራ ፍቅሯ፤
የተዋደቅሁላት – ለዳር ለድንበሯ፤
እኔ ለኢትዮጵያ – ካልበቃሁ ለአፈሯ፤
#በቁም_ሞቻለኋ – ዝምባብዌ ልቀበር?
ስማ እንጅ ጎረምሳው – አብቃኝ ላገሬ አፈር።
.
ኬኒያ የሄዱ፣ ሱዳን የታሰሩ፤
ባሕርም ተሻግረው፣ አረብ የታጎሩ፤
ተፈቱ አሉ ባንተ – እንዲህ ነው ጀግንነት፤
አሁን ገና ረካሁ – ልጄ አንተ ነህ በውነት።
‘ለአንድ ኢትዮጵያዊ
ሃምሳ ሱዳናዊ……’
ጠይቄ እንደነበር – መቼም አንተ አትረሳ፤
ተንቆ የነበር – የዜግነት ክብር – ያው ባንተ ተነሳ!
በዚህ በዚህ በርታ – እሰይ የእኔ አንበሳ።
.
“ኢትዮጵያዊ ሲሞት – ኢትዮጵያ ይሆናል፤
ከአፈሯ የበላ፣ በክብር ከፍ ብሎ፣ ራሷን ያክላል”
ያልኸውም አባባል – የምስማማበት ነው፤
አቅፌ በሳምሁህ – ባገኘሁህ ምነው !
.
የጫካ ወንበዴ – በሰራብኝ ሴራ፤
በሰው ሀገር ስኖር – ተጋብቼ ግራ፤
የኢትዮጵያዊነት – የዜግነት ነገር፤
ለቅጽበት ከዓይኔ ጠፍቶ አያውቅም ነበር።
.
በውስጥ አዳሃሪ – በተፈጠረ ጠብ፤
እርምጃ ስወስድ – ነገሩን ለማርገብ፤
ምንም ብዙ ዜጋ – ቢገደል በደርጉ፤
ጠፍቶኝ አልነበረም…
የዜግነት ክብሩ – ያገር ፍቅር ጥጉ።
.
በልማ መልሰኝ – ላይህ ጓጉቻለሁ፤
ብዙ የምመክርህ – ቁም ነገር ይዣለሁ።
.
አንድ ነገር ልንገርህ…
እኔ የምልህን – ብትሰማም ባትሰማም፤
ባድመን ለመስጠት – ቅንጣት አልስማማም፤

ጆሮህ ይህን መስማት – ቢወድም ባይወድም፤
ከኢትዮጵያ መሬት…. አንዲት ኢንች አትሄድም።
.
አንድ ምሥጢር ልንገርህ…
ላገሬ አብቃኝ እንጅ – ብቻ አንተ እኔን፤
ልኩን ነው ማሳየው – ሻዕቢያና ወያኔን።
(በእነ አሜሪካ ሸፍጥ – ሀገሬን ብለቅም፤
እጄንማ ያውቃል… የማንም ልቅምቅም!)
.
እንቅጩን ልንገርህ….
ባድመን አይደለም – ኤርትራም ራሷ፤
በፍጹም አይቀርም – በግድ መመለሷ።
.
ውይ ውይ እረስቸው – ለካን አንተ ነህና
በይቅርታ ምትሄድ….. በፍቅር ጎዳና….
ታውቃለህ አንዳንዴ – ወኔየ ይመጣል፤
ስሜቴ ሲተኮስ – ነገሬ ያመልጣል።
.
እኔን ታውቀኝ የለ…
“ግራህን ለመታ – አፍንጫውን በለው፤
ንቆ ሚሰድብህን – አሳደህ ግደለው!”
……የሚል መርህ አለኝ….
…….ባክህ ይቅር በለኝ……
.
የድሮው ወኔዬ…
አልሞትም ብሎ እንጅ፣ አሁንማ አርጅቼ፤
ዕድሜ አስጎንብሶኛል…
እግዜር ይቅር ቢለኝ፣ ንሰሐ ገብቼ፤
ማለፍ ነው ምፈልግ…
የበደልኋቸውን ይቅርታ ጠይቄ፣ ካስፈለገም ክሼ፤
መሞትን እሻለሁ፣ ወደ ኢትዮጵያ፣ አሁን ተመልሼ።
.
የትናንቱ ሕፃን – ደግሞስ አንተ ዛሬ፤
የይቅርታ ምዕራፍ – ስትከፍት በሀገሬ፤
እኔ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ፤
ይህንን ልቃወም አልችልም በግሌ።
.
ብቻ ኢትዮጵያን…
በድያት ከሆነ… ሕይወቴንም ክሼ፤
ማለፍ ነው ምኞቴ…
ወደ እናት ሀገሬ – አሁን ተመልሼ።

በዚሁ አጋጣሚ…
ለኢትዮጵያ ሕዝብ – ውለታ ዋልልኝ፤
ኮከቡን ተውና…
ንፁኋን አርማችን – ከፍ ከፍ አርግልኝ።
.
አየህ የእኔ አንበሳ…
የሀገር አንድነት – ዝም ብሎ አይመጣም፤
የጀግንነትም ክብር – ከሰንደቅ አይወጣም።
የክልል፣ የብሔር… ብሎ ነገር የለም፤
ሰንደ ዓላማችን – አንዲት ናት ዘላለም!!!

እስከምንገናኝ በል – ደህና ሁንልኝ፤
አደራ ኢትዮጵያን – አፈሯን ሳምልኝ!!!
—–//—–

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew