Daniel Kibret

የለውጥ ሂደት ሦስት ጉልቻዎች / ዲ/ን ዳንኤል ክብረት

የለውጥ ሂደት ሦስት ጉልቻዎች / ዲ/ን ዳንኤል ክብረት

አለቃ ገብረ ሐና እንዳስተማሩት ምርጥ ግንባታ ሦስት ነገሮችን ይፈልጋል፡፡ ሠሪ፣ ደንጓሪና አነዋሪ፡፡ የሀገር ግንባታም እንዲሁ፡፡ በሂደቱ ውስጥ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ዕውቀታቸውን ሠውተው ሌት ተቀን የሚሠሩለትን ይሻል፡፡ የእግር ኳስ ጨዋታ ሁለመናቸውን በሜዳ ላይ የሚያፈሱ ምርጥ ምርጥ ተጨዋቾችን እንደሚፈልገው ሁሉ፡፡ ሀገራዊ ለውጥ ስለፈለጉት፣ ስለናፈቁትና ስላጨበጨቡለት አይመጣም፣ ቢመጣም አይሳካም፡፡ የለውጡን ተውኔት በሚገባ የሚጫወቱ ምርጥ ተዋንያንንም ይፈልጋል፡፡ በየመዋቅሩ ገብተው፣ በየሥራ መስኩ ተሰልፈው፣ በየኃላፊነቱ ተሰይመው የሚዘውሩ ሠሪዎችን ይፈልጋል፡፡ እነዚህ ገንቢዎች እንዲሁ ሥራ ፍለጋ የሚከማቹ እንጀራ ፈላጊዎች አይደሉም፡፡ዕውቀትና እውነት የሚመራቸው ጠቢባን ናቸው እንጂ፡፡ ዕውቀትና እውነት የማይመራው የሀገር ግንባታና ሀገራዊ ለውጥ ብርሃንና መንገድ በሌለበት ገደላ ገደል እንደመጓዝ ያለ ነው፡፡ ዕውቀት ብርሃን፣ እውነትም መንገድ ነውና፡፡ ያለ ዕውቀትና እውነት የሚሠማሩ ሀገር ገንቢዎች ‹የሚከፈላቸው አጥፊዎች› ማለት ናቸው፡፡

ለውጥ ምርጥ ሠሪዎች ስላሉት ብቻም አይሳካም፡፡ ደንጓሪዎችንም ይፈልጋል፡፡ የደንጓሪ ሥራው ለግንባታ የሚሆነውን በቂና ተስማሚ ዕቃና መሣሪያ ማቅረብ ነው፡፡ ሀገራዊ ለውጥም ለለውጡ ዕውቀትና ክሂሎት የሚያቀርቡ ደንጓሪዎች ያስፈልጉታል፡፡ ዕውቀት የማይመራው ሀገራዊ ለውጥ፣ መሪጌታ እንደማይመራው ማኅሌት ድብልቅልቁ ይወጣል፡፡ እነዚህ ደንጓሪዎች ሀገር ግንባታ ምን እንደሚያስፈልገው፣ ለውጥ እንዴት እንደሚከወን የላቀ ዕውቀት ያላቸው፣ ምስጢር ያደላደሉ በያንያን ናቸው፡፡ በዕውቀት ጉዞ ውስጥ ሰባት ምዕራፎች አሉ፡፡ መማር፣ ማወቅ፣ ማንጠር፣ መጠንቀቅ፣ ማደላደል፣ መራቀቅና መበየን፡፡ ‹መማር› ማለት አንድን ነገር ለማወቅ መጀመር ነው፡፡ ‹ማወቅ› ደግሞ የተማሩትን ለመረዳትና ለማገናዘብ መብቃት፡፡ ‹ማንጠር› የዕውቀትን ግራ ቀኝ ተረድቶ የሆነውን ከሚመስለው፣ የተረጋገጠውን ከተለመደው፣ ባለማስረጃውን ከሚወራው አንጥሮ ለመለየት መቻል ነው፡፡ ከአንጉላው ነጥሮ እንደሚለይ ወለላ ቅቤ፡፡ ‹መጠንቀቅ› ማለት ክፉና ደጉን ለይቶ በዕውቀት ሂደት ውስጥ ስሕተትና ጥፋትን ላለመሥራት የሚበቁበት፣ከአላዋቂ ድፍረት ወደ ዐዋቂ ጥንቁቅነት የሚሻገሩበት ደረጃ ነው፡፡ ‹ማደላደል› የተለያዩ የዕውቀት ዘርፎችን ከየመስኩ ቀስሞ፣ አጋጭቶና አፋጭቶ፣ አነጻጽሮና አስተያይቶ፣ አፎካክሮና አወዳድሮ፣ አቀራርቦና አስማምቶ እውነትና እውነታ፣ ሐቅና መርሕ ላይ የሚደረስበት እርከን ነው፡፡ ይህንን ሁሉ ያለፈ ሊቅ በመጨረሻ ‹በያኒ፣ መበይን› ይሰኛል፡፡ እርሱ ራሱ እንደ ሕግ እንደ መጽሐፍ ይጠቀሳል፡፡ የሚለግሰው ሐሳብ፣ የሚሰነዝረው አስተያየት፣ የሚሰጠው ፍርድ፣ የሚያቀርበው ትንታኔ ፈራጅ፣ ዳኛ ይሆናል፡፡ ‹እገሌ ብሏል› ተብሎ ይጠቀሳል፡፡ እርሱ ዐዋቂ ሳይሆን ዕውቀት ሆኗል፡፡
ሀገር እንዲህ ያሉ ደንጓሪዎች ትፈልጋለች፡፡ እንደነዚህ ባሉ ዐዋቂዎች ምክር፣ ዕውቀት፣ ብያኔና ሐቲት የምትገነባ ሀገር ቢነቀንቋት አትፈርስ፣ ቢያናጓት አትሰነጠቅ፣ ቢገዘግዟት አትወድቅ፡፡ ሠሪዎቿም በልማድና በመሰለኝ፣ በመመሪያና በክድርና ከመሥራት ይልቅ በዕውቀትና በእውነት እንዲሠሩ ያስችሏቸዋል፡፡ እንዲህ ያሉ በያንያን ያሏት ሀገር እንደ አይጥ መሞከሪያ አትሆንም፡፡ እንደ ዕቃ ዕቃ ተጨዋች እያፈረሰች አትሠራም፡፡ ለዕውቀትና ለዐዋቂ ቦታ የሌላት ሀገር ጨለማ እንደ ብርድ ልብስ፣ ድኅነትም እንደ ቡልኮ ሞቋት፣ ተኝታ ለመኖር ወስናለች ማለት ነው፡፡
ሠሪና ደንጓሪ ያሏት ሀገር አንድ ይቀራታል፡፡ አነዋሪ፡፡ አቃቂር አውጭ፣ ሐያሲ፣ ተች፣ ሞጋች፣ በንሥር ዓይኑ እያየ በመንጠቆ ጣቱ የሚያወጣ፡፡ ሳይፈራና ሳያፍር፣ ሳያደላና ሳይወግን ለእውነት የሚሟገት አነዋሪ፡፡ ሠሪና ደንጓሪ ያልታያቸውን በልዩ ዓይኑ የሚያይ፣ ስል፡፡ ጠላው ከነአተለው፣ ጠጁ ከነአምቡላው፣ ስንዴው ከነ ገለባው፣ ወተቱ ከነ አሬራው እንዳይጓዝ በትኖ የሚያሳይ፡፡ ከፍ ብለው አንገቴን ዝቅ ብለው ባቴን ይቆርጡኛል ሳይል ዐመዱን ነጭ ከሰሉን ጥቁር የሚል፡፡ እንዲህ ያለውን አነዋሪ ያገኘች ሀገር ቆሻሻዋን እያጠበች፣ዝገቷን እያራገፈች ትጓዛለች፡፡ የትናንት ችግሯ ለዛሬ፣ የዛሬ ስሕተቷ ለነገ ማነቆ አይሆናትም፡፡
አንዲት ሀገር ግንባታዋ የተዋጣ እንዲሆን ከማንም በላይ ለአነዋሪዎቿ ጥብቅና መቆም አለባት፡፡ ከሁሉ የሚበልጥ ጥቅም ስላላቸው አይደለም፡፡ ከሁሉ የሚብስ መከራ ስላለባቸው እንጂ፡፡ ማንም ሰው በጠባዩ አመስጋኙን እንጂ ተቺውን አይወድም፡፡ በተለይ ደግሞ ሥልጣን፣ ጉልበትና ገንዘብ ያለው አነዋሪዎቹን በጉልበቱ ደቁሶ፣ በሥልጣኑ ደምስሶ፣ ገንዘቡንም አልሶ፤ ቢቻል ማጥፋት ባይቻል ዝም ማሰኘት ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው ከሁሉም በላይ አነዋሪዎች ጥበቃ የሚገባቸው፡፡
ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ እንደ ዋልያ ቀና ብላ እንድትሄድ ከፈለግን – ሠሪም፣ ደንጓሪም፣ አነዋሪም ያስፈልጉናል፡፡ ከሦስቱ አንዱ ጉልቻ ከጎደለ የተጣድንበት ድስት ሁላችንንም ይዞ ይደፋል፡፡

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew