Two Sinod of Ethiopia

የቀኖና ጥሰቱ በኹለቱም ሲኖዶሶች የኾነ ነው / ዲ/ን ዓባይነህ ካሴ

የቀኖና ጥሰቱ በኹለቱም ሲኖዶሶች የኾነ ነው / ዲ/ን ዓባይነህ ካሴ
በውጭ ሀገር ከሚገኘው ሲኖዶስ አንድ የወጣች በጎ ቃል አለች፡፡ እርሷም “የቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ጉዳይ ያሳሰበውና በበጎ ፈቃደኛነት የተቋቋመው የኹለተኛው ዙር የሰላምና አንድነት ኮሚቴ በኹለቱም ሲኖዶሶች መካከል ያለውን የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት በሰላም እንዲፈታ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ በተለያዩ ብዙኃን መገናኛ ሲገለጽ የቆየ መኾኑ ለኹላችንም ግልጽ ነው” የምትል ናት፡፡
እዚህ ውስጥ “በኹለቱም ሲኖዶሶች መካከል ያለውን የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት” የምትለው ቃል ድንቅ ናት፡፡ እስከዛሬ ድረስ የነበረው መጓተት ቀኖና የጣስኸው አንተ ነህ አንተ ነህ የሚል ነበር፡፡ አሁን ግን ጥፋቱ የጋራ ነው የሚል መልእክት የያዘ መግለጫ መሰማቱ እርቀ ሰላሙን ብዙ ያራምደዋል፡፡ እውነቱ ያለው እዚህ ላይ ነውና! ወደ አንድ አቅጣጫ መጠቆም ሲያበቃ ነገር መክተቻውን ያገኛል፡፡
አንዱን ጻድቅ ሌላውን ኃጥእ የሚያደርገው መጠቋቆም እንደረፈደበት ከዚህ እናውቃለን፡፡ የውጭው ሲኖዶስ ይህን ያኽል እንደተጓዘ ሁሉ የሀገር ቤቱ ሲኖዶስም በዚህ ደረጃ ኾኖ ወደ ድርድሩ ሊገባ ይገባል፡፡ የጠፋ የተበላሸ ሁሉ በጋራ የጠፋ እንጅ ወደ አንድ ወገን ብቻ የሚላከክ አይደለም፡፡ ከሀገር ቤቱ ሲዶስ አባላት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ሰሞኑን እያሰሙት ያለው ድምፅ እጅግ አስፈላጊ እና ደረጃውን የጠበቀ ኾኖ ተገኝቷል፡፡ የውጭው ሲኖዶስ የቀኖና ጥሰቱ በኹለቱም መካከል ያለ ነው ማለቱም ብዙውን ጠመዝማዛ መንገድ ቀና ያደርገዋል፡፡
ከዚህ በተቃራኒ ሌላ የሚናገር ተልእኮው እርቀ ሰላሙን ማፍረስ ይኾናል፡፡ በአንድ ወገን ብቻ የሚነገርን ታሪክ መተረክ እውነተኛ አያደርግም፡፡ እዚያም ቤት እሳት አለ ነውና ነገሩ እሳት መጫጫሩ አሁን አይበጅም፡፡ ዓለማውያን እንኳ ሲደራደሩ ተኩስ ያቆማሉ:: ነገር ግን የእርቀ ሰላሙ ዋዜማ ብዙ ተስፋ ሰንቆ በሠናይ መዓዛ ታውዶ እየመጣ ሳለ ሌላ ሌላ የሚናገሩ ሰዎች እንዳሉ ታዝበናል፡፡ የነገሩ ዳር መድረስ የሚያስጨንቃቸው ሰዎች እንዳሉ መገመት አይከብድም፡፡
የዚህ ዙር እርቀ ሰላም መሳካት ብዙ ትርፍ ያስገኛል፡፡ በአንፃሩም አለመሳካቱ ብዙ ያጎድላል፡፡ ለጉድለቱ ምክንያት ኾኖ አለመገኘት የጊዜው መድኃኒት ነው፡፡ የእርቀ ሰላሙ እውን መኾን ልባቸውን የሚያርድባቸው በተንኮል የሚጓዙ መኖራቸው ሊሰወረን አይገባም፡፡ ከዚህም አልፈው ጥቅማችን ይነካል ብለው የደነገጡ አንዳንድ ሰዎች በሀገር ቤትም ኾነ በውጭ የተነጠለች ቤተ ክርስቲያን ይዘው ለመቀጠል የሚዶልቱ እንዳሉ ተደርሶበታል፡፡
ስለዚህ የእርቀ ሰላሙ ጉዞ እንደዚህ ያሉ አደናጋሪ አካሔዶች ድራሻቸውን እስከማጥፋት ሊዘልቅ ይገባዋል፡፡ ከተሰጠው መግለጫ ውጭ እያፈነገጡ እንደ አዲስ የመለያየትን ገደል የሚቆፍሩ መኖራቸውም ቀላል ግምት ሊሰጠው አይገባም፡፡ የዋሽንግተን ዲሲ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ለመቀላቀል የወሰደችው እርምጃ የሚወደድ እና በአሁኑ ሰዓት የሚፈለግ የመኾኑን ያኽል እንደዚህ ከመሰለው የሰላም ጉዞ ለማነቀፍ የሚጣጣሩ አፈ ጮሌዎች በሌላ ጎራ መኖራቸው ደግሞ ያሳስባል፡፡ ምናልባትም ይህ ይደርሰብኝ ይኾን ብሎ ከመስጋት የመጣ ሊኾን ይችላል፡፡ የእርቀ ሰላም ጉባኤው ሊጀመር ዐሥር ቀን ሲቀረው ጀምሮ በተከታታይ ይኹነኝ ብሎ ነገር መዘብዘቡ የስጋት ውጤት ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች ውርውር ይበሉ እንጅ የውጭው ሲኖዶስ እጅግ አስመስጋኝ እና ታሪካዊ ቃል በማስቀመጥ አፈ ጮሌዎችንም ይሁን ሌላ ተንኮል ያቀዱትን ኩም አድርገዋቸዋል፡፡ የሚፈለገው ይህ ነው፡፡ ለእርቀ ሰላሙ የተከፈቱትን በሮች መልሰው ለማዘጋት መድከማቸው ሊያፍሩበት ይገባል፡፡ እስከ ዛሬ ባልተናገሩት መጠን ከፍ ባለ ጩኸት ሰላሙን ለመረበሽ በአደባባይ ብዙ ጸያፍ ቃል እያሰሙ መኾናቸው የቤተ ክርስቲያንን ልጆች ሊያደናግራቸው አይገባም፡፡ እርቀ ሰላሙ ይቀጥላል፡፡ እነዚህም ይጮኻሉ፡፡ ዕድላቸውን ቢጠቀሙበት ዕድለኛ ያደርጋቸዋል፡፡ በእነርሱ ምክንያት የሚደናቀፍ ነገር ግን የለም፡፡
እነዚህን ዝርዝር ነገሮች ለማንሣት ጊዜው አይፈቅድልንም፡፡ ተኩስ ባቆምንበት ወቅት ነባርና አዳዲስ ወታደሮች ወረራ መጀመራቸውን ስለ እርቀ ሰላሙ ብለን ለመታገስ ተገድደናል፡፡ ልበ-ወለድ ነገር ታሪክን አያክልም፡፡ እርቀ ሰላሙ በእነዚህ ውርውር ባዮች መደናቀፍ የለበትም፡፡ እንዳልተሰማ ቆጥረን ቁም ነገሩን ማካሔድ ይጠበቅብናል፡፡

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew