Anti Amhara Spirit

የአማራ-ጠልነት መንፈስ ሲወርድ ሲዋረድ

(መላኩ አላምረው)

—›

የአማራ-ጠልነት ጠንሳሽ ጥልያን ነች። ‹‹ጣልያን ደግሞ አማራን ለምን ጠላችው›› ብላችሁ እደማትጠይቁኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በ5 ዓመቱ ጦርነት ወቅት ከ95 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ አርበኞች በጎጃም፣ በሸዋ፣ በጎንደርና በወሎ ብቻ ይገኙ እንደነበር ማስታወስ በቂ ነውና፡፡ (ፕ/ር መስፍን ከ85 በመቶ በላይ አርበኞች እነ በላይ ዘለቀን መሪ አድርገው ጎጃም ላይ ተጋድሎ እንዳደረጉ ጽፈዋል፡፡)

የጣልያን ክፋት አማራ-ጠልነቷ አልነበረም። ይህን መንፈሷን ለሀገር በቀል ‹‹ነፃ አውጭ ነን›› ባይ ድርጅቶች ማጣባቷ እንጅ። የእርሷ አማራ-ጠልነት በራሷ ብቻ ቢቆም ኖሮ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ስትሸነፍ አብሮ በቆመ ነበር። ግን ፋሽታዊ ጦሯ ቢሸነፍም ክፉ መንፈሷ ይቀጥል ዘንድ ለሰሜን/ኤርትራ በቀል ድርጅቶች ቀስ እያደረገች አዋረሰች። በኤርትራ በረሃ ያገኘችው ጀብሃ የመጀመሪያ የመንፈሷ ማረፊያ ነበር። አማራን ከክርስትና ጋር አያይዛ ክፉ ሰይጣን አድርጋ ሳለችለት። ጀብሃም መሠረቱ እስልምና ነበርና እውነት መሰለው። ክፉ መርዟን በሃይማኖት ሸፍኖ ዋጠላት።

……ጀብሃን ለመደምሰስ የተቋቋመው ሻዕቢያ… ከጀብሃ ጋር ለስለላም ለድለላም አብሮ ሲባጅ ይህ አማራ-ጠልነት ተጣባበት። ጀብሃን ሲደመስስ መንፈሱን ወርሶ ቀረ።

-›

ሻዕቢያም ይህን መንፈስ ተሸክሞ በረሃ ሲወርድና ተራራ ሲቧጥጥ ሌላ የመንፈሱ ተጋሪ አገኘ። በቅድስት ምድር ትግራይ ክፋትን ፀንሶ የበቀለና አማራን ለመበቀል የተሰለፈው ሕወሓት ገና ዳዴ ሲል ተገናኙ። ሻዕቢያ ለሕወሓት ከጦር ስልት/ስትራቴጂ በላይ አማራን በጠላትነት መሳልን አለማመደው። ሕወሓት ጥሩ አድርጎ አሳደገው። የአማራ ጠልነት መንፈሱ ትሕነግ ላይ ሲደርስ ጎለመሰ። በማታገያ ማኔፌስቶም ተረቅቆ ሰፈረ።

ሕወሓት ይህን መንፈስ ብቻውን መሸከሙ አላስችል አለውና ሌላ ተጋሪ ፍለጋ ተንከራተተ። ኦነግን አገኘው። ኦነግ እንደዚህ ተመችቶት የተቀበለው መንፈስ አልነበረም። በዚህ መንፈስ በተጠመቀ ማስት አማራን ‹‹የኦሮሞ ቅኝ ገዥና ጨቋኝ›› ብሎ አወጀበት።

—›

የጣልያን አማራ-ጠልነት መንፈስ በጀብሃ ስር ሰዶ በሻዕቢያ ቅጠል አወጣ። በሕወሓትና በኦነግ ፍሬ አፈራ። ስማቸውም ትሕ(ነግ) እና ኦ(ነግ) የሆነው ከአማራ ጋር ለዘለቄታው ለመዋጋት ነው። ነፃ አውጭ ግንባርነታቸው በአማራ ላይ ለመዝመት እንጅ ሀገራችንስ ዕድሜ ለአባቶቻችንና ነፃ ምድር ነበረች። ‹‹ነፃ አውጭነታችን ከደርግ አምባገነናዊ ሥርዓት ለመላቀቅ ነው›› የሚሉት ውሸታቸውን ነው። ደርግንማ አማራም ተዋግቶታል። በደርግማ ከአማራ በላይ አልተበደሉም። ደርግም ከአማራ በላይ የጨፈጨፈው አንድም ብሔር የለም። ትሕነግ/ሕወሓትም ሆነ ኦነግ ሕዝባቸውን ነፃ ለማውጣት ግንባር የፈጠሩት አማራን ጠላት በማድረግ ነው። ደርግን አይደለም። ደርግን ቢሆን ኖሮማ…. ደርግ እንደተሸነፈ ስማቸውንም ግብራቸውንም በቀየሩ ነበር። ጠባቸው ከደርግ ሳይሆን ከአማራ ሕዝብ ጋር ስለሆነ ግን ነፃ አውጭነታቸውን ላለፉት የአማራ-የመከራ ዘመናት ሁሉ ይዘውት ነው የቀጠሉት። ከደርግ ወታደሮች በላይ አማራን እያሳደዱ በጅምላም በተናጠልም አሳደዋል፤ አፈናቅለዋል፤ ገድለዋልም። (ፈጣሪ ለአማራ ሲያዳላ ሕወሓትና ኦነግ ያኔ በጧቱ ተጣሉለት እንጅ እንደመጀመሪያው አያያዛቸው ተባብረው እስካሁን ከከፈለው ዋጋ እጥፍ ያስከፍሉት ነበር። እርግጥ አሁንም ለአማራ ሲሉ መታረቃቸው አይቀርም።)

—›

ባለፉት ከ50 በላይ ዓመታት የተቀነቀነው ፖለቲካ ዋና ማጠንጠኛ ይኸው ነበር። አማራ-ጠልነት። የካድሬ ማሰልጠኛ ሰነዶች በሙሉ ይህን ይመሰክራሉ። መግቢያቸውም መደምደሚያቸውም “የትምክህትና የነፈጠኛ ሥርዓትን” ስለማስወገድና ርዝራዡንም ስለማጥፋት ነው። ርዝራዡ የሚባለው የአማራ ሕዝብ በጠቅላላ ነው።

(በመሠረቱ ሕዝብን በጠላትነት የፈረጀ ድርጅት በወንጀል መጠየቅ ነበረበት። ሕዝብ ጠላት አይደረግም። ትሕነግ በግልጽ ‹‹ጨቋኟ የአማራ ብሔር›› የሚል ፍረጃ እስቀምጣ ነበር፡፡ ነውርና ፀያፍ ነው። ግን ትሕነግ በይፋ ሰንዳ በጠላትነት የዘመተችበት አማራ ይህ ነውር ተፈፅሞበታል። ለዚህ ሊካስ ይገባው ነበር። እንኳን ሊካስ እርሱን የሚጠሉት መልካቸውን እየቀያየሩ ቀጥለዋል።)

ባለፉት የኢህአዴግ የግዛት ዘመናት ሁሉ የወጡ ፖለሲዎችም ሆኑ ሌላ ሰነዶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአማራ ሕልውና ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ። የእያንዳንዱን ሰነድ መግቢያ ብቻ ተመልከቱና ፍረዱ። ‹‹ትምክህተኛና ነፍጠኛን›› ያወግዛል። ይጠፋ ዘንድም ይሠራል። በመሠረቱ ግን ትምህትና ነፍጠኝነት የአማራ ሕዝብ የማንነት መሠረቶች እንጅ የስድብ ስሞች አልነበሩም አይደሉምም። ለአማራ “ትምክህት – በአንዲት ሀገርና በአባቶቹ ጀግንነት መመካት” እንጅ ሌላ አይደለም። ጠላቴ ያሉት እንደተረጎሙለት “ከቾቪኒዝም” ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ ስነ ለቦና ነው። ነፍጠኝነትም ለሀገር ዳር ድንበር የመዋጋት የጀግንነት ስነ ልቦና እንጅ የገዛ ወገንን ከመጨቆን ጋር ፈጽሞ አይያዝም። እነዚህ መገለጫዎች አማራ ሊኮራባቸውና እጥብቆ ሊይዛቸው የሚገቡ በጎ መገለጫዎቹ ሆነው ሳለ በጠላትነት በተነሱበት ኃይሎች ስድብ ሆነው ቀረቡለት። እንዲጥላቸውም ሲገመገምባቸው ኖረ። መሪ ይሆነው ዘንድ የተፈጠረለት ድርጅትም ሳይቀር አማራን ማድከሚያ ነጥብ አድርጓቸው ነበር።

—›

የአማራ-ጠልነት መንፈስ ሲወርድ ሲዋረድ አሁን ላይ ደርሷል እንጅ የትም አልቆመም። አሁን ላይ ከአማራ ውጭ ያሉት ፖለቲካዊ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች ይህ መንፈስ የተጣባቸው ናቸው። አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የመንፈሱ ሰለባ ሆነዋል። ሁሉንም ታዘቧቸው። ‹‹አማራ›› የሚል ስም ለመጥራት ይንቀጠቀጣሉ። በአማራ ስም የሚመጣ ምንም ነገር ያማቸዋል። የአማራ ፓርቲ፣ የአማራ ማኅበር፣ የአማራ ቅርስ…. ሁሉ እንዲኖር አይፈልጉም። ሰላም የማይሰጣቸው ስም ቢኖር አማራ ነው። ወደው እንዳይመስላችሁ። የተጣባቸው መንፈስ ነው። ክፋቱ መንፈስ ሲጣባ አይታወቅም። መቼ እንዴት እንደተዋረሳቸው አያስታውሱትም። ግን በተግባር ሲገልጡት ይታያሉ።

—›

የአማራ-ጠልነት ክፉ መንፈስ ባይኖር ኖሮ… አማራን ለምን ይጠሉታል? ምን አጥፍቶ? አንድ ሀገርን መውደድ ጥፋት ሆኖ? ለነፃነት መዋደቅ ክፋት ሆኖ? በዘር በድንበር ሳይታጠሩ መኖር ወንጀል ሆኖ? ለምን?

መንፈሱ ስላለባቸው አማራን ያለ ስሙ ስም ያለ ግብሩም ግብር እየሰጡ ይጠሉታል። ከ80 በላይ ማንነቶች ተጠብቀው በኖሩባት ሀገር ጨቋኝና ጨፍላቂ አድርገው የሌለ ማንነት ሲሰጡት ሐቅ ሆኖ ሳይሆን የመንፈሱ ውጤት ነው። እንጅማ… እንደ አማራ የሌሎችን ማንነት ከማክበርም አልፎ የሚጠብቅ የትም አልነበረምም የለምም።

-›

አማራ ‹‹አንድ ባህል አንድ እምነት…›› ምናምን ይላልና ለሕብረ ብሔራዊነት አደጋ ነው ብለውም አስወርተውበታል፡፡ ይህ ቅጥፈት ነው፡፡ ይህን ብሎ አያውቅም፡፡ ዝም ብሎ ወሬ ነው፡፡ በተግባር የሌሎች ማንነት ተከብሮ የሚኖረው በአማራ ክልል ነው፡፡ በአማራ ክልል ማንም ልዩ ማንነት ያለው ራሱን በራሱ ነው የሚያስተዳድረው፡፡ አማራ ማንንም እንደ ባዕድ አያይም፡፡ ሁሉንም እንደራሱ አክብሮ ነው የኖረው፡፡ አማራ ነው በሌሎች ክልሎች ማንነቱ ያልተከበረለት እንጅ የማንንም ማንነት አልተቃወመም፡፡ እንዲህ ብለው የሚከሱት ጠላት ሊያበዙበት የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በተግባር ሌሎች ብሔሮች ናቸው ጨቋኝ፡፡

እንደሚያወሩት አማራ ‹‹አንድ ባሕል አንድ እምነት አንድ ቋንቋ… ›› ቢፈልግ ኖሮ… ኢህአዴግ ሲገባ ማንነታቸው ተከብሮ የተገኙት ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ከቻይና ነው እንዴ ‹‹ኢምፖርት›› የተደረጉት??? አማራው በትንሹ ለ500 እና ከዚያ በላይ ዓመታት በመራት ሀገር የ80 ብሔርሰብ መገኘት የአማራን ማንነት አክባሪነት አያሳይም? ከተግባ ይልቅ ወሬ ስለሚንጠን አማራን ‹‹ጨቋኝና ጨፍላቂ›› አድርገን የሰደብን ሁሉ ሐቁን መሬት ላይ እዩት፡፡ እንኳን በሌላው ክልል በራሱ በአማራ ክልል ማንም ማንነቱ ተከብሮ ነው የኖረው፡፡ አሁን በአንዳንድ ማንነቶች ዙሪያ ችግር የመጣው ሌላ አላማ ያለው አካል ‹ፖለቲሳይዝድ› ሲያደርገው ነው፡፡

—›

ማንም አክቲቪስት ነኝ ባይ በአማራ ላይ አፉን ካልከፈተ አይሆንለትም። ኢትዮጵያን ለመምራት የሚመጡ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሰንደቋን የሚያመልከውን ለነፃነቷ በወደቁ ሰማዕታት ስም የሚምለውን ለዳር ድንበሯ የሚሞተውን አማራን ለምን ይጠሉታል?

-›

የሚገርመው እኮ አማራን ብቻ ሳይሆን አማራ የሚወደውንም መጥላታቸው ነው። የገዛ ሀገራቸውን ስም ኢትዮጵያን ለመጥራት የሚንቀጠቀጡት ሰንደቅ አላማዋን ከፍ አድርገው ለመያዝ የማይደፍሩት አማራ ስለሚወዳቸው ነው። አንዳንዶችማ… ሌላው ቀርቶ “ከእነርሱ ዘር” የተወለዱትን የሀገር ጀግኖች እንኳን አማራ ስለሚወዳቸው አይወዷቸውም። ግና ይህ ክፉ የአማራ-ጠል መንፈስ አይደለምን???

—›

መውጫ፦ ይህ ሐቅ ነው፡፡ ልብወለድም ተረትም አይደለም፡፡ አማራ-ጠልነት በሌሎች ብሔሮች ዘንድ የፖለቲካ መታገያ ስልት ሆኖ በትውልድ ቅብብሎሽ የቀጠለና ወደ ሥነ ልቦናነትም ከፍ እያለ የመጣ መሆኑን ለማሳየት… ለፌስቡክ እንዲመች ቀለል አድርጌ አቀረብሁት እንጅ በጥልቀት እያጠናት ያለ ጉዳይ ነው። ጽሑፉን በማስረጃ/ዋቢ በማጣቀስና በመሰነድ በሰፊው ለሕትመት አበቃዋለሁ። ይህን የማደርገው ወድጄ ሳይሆን… አማራን ባልዋለበት እያዋሉ፣ ያልሠራውን ክፋት እየፈጠሩ በትውልዱ ዘንድ እንደ-ጠላት በመሳል የፖለቲካ መታገያ ያደረጉ ድርጅቶች ስላሉና ‹‹የተሸነፈ ጠላት በፈጠረው የተሳሳተ ጥላቻ›› ሀገር ሊያፈርሱ ጫፍ ላይ ስለደረሱ ለሀገሬ መድኅን ይሆናት ዘንድ ሐቅን በመግለጥ የራሴን ድርሻ ለመወጣት የዜግነት ግዴታየም ስለሆነ ነው፡፡ አማራን በጠላትነት ፈርጆ ብሔራዊ መግባባትን ማምጣት አይቻልምና፡፡

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew