የአዲስ አበባው ‹‹ድጋፍ ለዐቢይ›› ሰልፍ ቅድመ ትንበያ

(መላኩ አላምረው)
—›

መስቀል አደባባይ የሚኖራት ድባብ በአጭሩ፡-


መስቀል አደባባይ በሕዝብም በማስታወቂያም ትጥለቀለቃለች፡፡ ምን አልባት ከባድ ዝናብ ከጣለ አደባባዩ ብቻ ሳይሆን መላው የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በጎርፍ ይጥለቀለቃሉ 🙂 ትልልቅ ባነር የተሸከሙ የሸነግ አባላትም በላብ ይጥለቀለቃሉ 🙁 (ኧረ ቀይ ባሕር ወስዶ ያጥልቅህ… የሚል የእርግማን ድምጽ ተሰማኝ፡፡ አርጎት ነው 🙂 ምነው ቀይ ባሕር በተለይም በአሰብ በኩል ለመሄድ ባበቃኝና በጠለቅሁ፡፡)
በሰልፉ የባነሩና የሰው ቁጥር እኩል ይሆናል። ባነር ያልያዘ ሰው አይኖርም። ሁሉም ባነሮች የዶ/ር ዐቢይን ፎቶ ይይዛሉ። ከፎቶው ግራ-ቀኝ፣ ራስጌ-ግርጌ የተለያዩ ምልክቶችና ቀለማት ይኖራሉ። ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው የቀለም ዓይነት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነው። ይህ የሚሆነው አብዛኛው ሰልፈኛ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ይዞ ስለሚወጣ ነውን? አይደለም። የኦነግ ባንዲራም ቀለማቱ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ በመሆናቸው እንጅ 🙂 🙁
በዚህች ዕለት ባለ ኮከቡን ባንዲራ የሚይዙ ብፁዓን ናቸው 🙁 እርግጥ ጥቂት አሸባሪዎችና ግብረ አበሮቻቸው ኮከብ ያለበትን ባንዲራ አቅፈው እንደሚይዙ አይጠረጠርም 🙁 ከፍ አድርገው ማውለብለብ ግን አይታሰብም።
በአብዛኛዎቹ ባነሮች ከተለጠፉ ምስሎች የጅቦች ይበዛል፡፡ ከየምስሎቹ ግርጌ ‹‹የቀን ጅብ›› የሚል ጽሑፍ ቢለጠፈም የጅቦቹ ፎቶ ግን በሌሊት ጨለማ ውስጥ የተነሱት መሆኑ ደብዛዛ ብርሃኑ ያሳብቃል 🙂
—›
ከተሰላፊዎች መካከል አንዳንዶቹ፡-

የሸነግ አባላት… ‹‹ሰገጤና የቀን ጅብ ይውደም፣ ዐቢይ ሸነግ ነው›› የሚሉ መፈክሮችን ይዘው መሐል አደባባዩን ይሰፍሩበታል። በየባነሮቻቸው የሚታዩ ቀለማት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ብቻ ናቸው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊነትን ለመስበክ ሸነግ መሆን ብቻ በቂ ነው›› የሚል በእጅ የተጻፈ ጽሑፍም ይዘዋል፡፡ የታዘዘው ባነር በመብራ መጥፋት ሳይታተም ቀርቶ መሆን አለበት 🙂

ዳንኤል ብርሃነ… ጥርሱን ነክሶ ወጋገን ባንክ አዲሱ ፎቅ ላይ ወይም ግዮን ሆቴል ግቢ ዘንባባ ተከልሎ ይቆማል 🙂 ‹‹ለሆርን አፊየርስ›› የሚሆን ቀረጻ ተደብቆም ቢሆን ይቀርፃል/ያስቀርፃል።

አከራዬ ጋሽ ጣሰው… ‹‹ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ይመለሱ›› የሚል መፈክር ይዘው ይገኛሉ 🙂 (ጋሽ ጣሰው የደርግ ወታደር እንደነበሩ ታውቃላችሁ፡፡ ሁሌም ሕልማቸው ጓድ ሊቀመንበር ወደ ሀገር መጥተው እርሳቸውን አልቅሶ መቅበር ነው፡፡ ‹‹ምን ጥፋት ቢኖርበት… እንቅል ባጣላት ሀገር በክብር ቢቀበር ምናለበት… በሰልፍ የተቀበረ ሁሉ ጥፋ የለበትም ወይ?›› ይላሉ – ስለ ቀብር በተነሳ ቁጥር፡፡ ጋሽ ጣሰው የሰፈራችን ማለቴ የሰፈራቸው ዕድር ቀብር አስፈጻሚ ናቸው፡፡)

የቦሌ ቀበጦች… ‹‹ዐቢይዬን መቃወም #ሼም ነው! ዱ ኖት ሃራስ ዐቢይዬ! ሀገር መስት ቢ ፈሪ ኤንድ ፍሪኪ›› የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ከእስጢፋኖስ ወደ ቦሌ በሚወስደው መንገድ ጥግ ይዘው ይቆማሉ። ሲጨፍሩ አይታይም፡፡ ምክንያቱም የአማርኛ ሙዚቃ ምኑም አይመስጣቸውም 🙂

የፌስቡክ አሽሟጣጮች…. አሳዬ ደርቤ (AssayeDerbie) ና አንዷለም በውቀቱ (AndualemBuketo)… ሽሙጥ ለመጻፍ የባቡር ሐዲዱ ድልድይ ላይ ወጥተው ቆመዋል 🙂 በላይ (BelayBekele) ‹‹ግጥም ለመጻፍ ባቡር ሐዲድ ላይ መሰቀል አያስፈልገኝም›› ብሎ ከስር የድልድዩን ተሸካሚ ምሶሶ ተደግፎ ቆሟል፡፡ ስመኝ ታደሰ (Zewdie TadesseSimegn) በመገረም ግራ ቀኝ እያየች #ከመስ ደመወዝ ጋር ቆማለች፡፡ መስ ደመወዝ የሰልፉን ታሪካዊ አንድምታ ለመተንተን እያቀደች ነው፡፡ ሌሎችም የፌስቡክ ፈርጦች በየሰልፉ መሐል አሉ፡፡ አብዛኞቹ የሰልፊ ፎቶ ተነሽዎች የሰልፉን ስርዓት ትንሽ እየረበሹት ይመስላል፡፡ ‹‹ሰልፍና ሰልፊ›› ተጣጥሞ መሄድ አልቻለም፡፡
….
ከአደባባዩ በስጀርባ፡-

ግዮን ሆቴል ውስጥ እነ አቦይ ስብሐትና እነ ዓባይ ፀሐዬ እንዲሁም እነ በረከት ስምዖን ደረቅ ውስኪ አስቀርበው አሁንም አሁንም ይጠጣሉ። እንደ ድሮው ግን #ቺርስ አይባባሉም 🙂

ዶ/ር ዐቢይ በቤተ መንግሥቱ ሆኖ ሰልፉን ‹ላይቭ› ይከታተላል። ከጥቅሶች መካከል ‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኤርትራ›› የሚል አለመያዙን ሲያረጋግጥ ፈገግ ይላል። ከዚያም አንድ ቀን አስመራ ብሄድ ብሎ ምን እንደሚናገር ማሰብ ይጀምራል።

ኃይለማርያም ደሳለኝ… ዜናው ዘግይቶ ስለደረሰው ‹‹ምን አይነት ሰልፍ ይሆን? እኔን ይመለስ እንዳይሉኝ ብቻ›› እያለ ይጨናነቃል። ወ/ሮ ሮማን ሰልፉ ለዐቢይ ድጋፍ መሆኑን ስትነግረ…. ‹‹አንች ነሽ ልቀቅ ብለሽ… ይህኔ ይህ ሰልፍ የእኔ ነበር ሚሆነው›› ይላታል። እርሷም… ‹‹ልክ ነህ… ግን ሰልፉ የድጋፍ ሳይሆን የይውረድልን ተቃውሞ ነበር ሚሆነው›› ስትለው ይደነግጥና “በኢየሱስ ስም” ብሎ ዝም ይላል:)

ዶ/ር ደብረ ጽዮን መቀሌ በቢሮው ቁጭ ብሎ…. ለትግራይ ቴሌቪዥን ሰልፉን እንዳይዘግቡ የሚያስጠነቅቅ ደብዳቤ ይጽፋል። ጌታቸው ረዳ ግን ቢሮውን ለቆ ወደ በርጫ ቤት ይሄዳል። አንድ ሰውም አብሮት አለ…. አብርሃ ደስታ መሰለኝ… ከጀርባው ነው የሚታየኝ።

ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ… በሰልፉ ላይ ግንቦት ሰባትን የሚደግፉ መፈክሮች አለመኖራቸውን ሲያውቅ ይበግናል፡፡ ቢያንስ ‹‹ዶ/ር ብርሃኑ የመነፃነት ታጋያችን ነው›› የሚል መጥፋቱ ያበሳሏል፡፡ ግንቦት 7 አማራን በአሸባሪነት ለማሰር ሲፈለግ ብቻ የሚለጠፍ ታርጋ መሆኑ አልገባውም ልበል ?

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew