የዶክመንታሪ ሚናና “ምናባዊው…”

የዶክመንታሪ ሚናና “ምናባዊው…”

(Asemahegn Asires – Journalism Instructor)

“ምናባዊው…” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ዘጋቢ ዶክመንታሪ (Expository Documentary) በጭብጡ እና ይዘቱ የበዛውን ሕዝብ ከማስደመም አልፎ አሳዝኗል፤ አስለቅሷል፡፡ እንዲህ ያለ ታምር በሆሊውድ ፊልሞች እንኳ አላየንም፡፡ ምን ያለ ዝቅጠት፣ ምን ያለ የቁም ሞት፣ ምን ያለ ብልግና፣ እንዴት ያለ ቀውስ ውስጥ እንደገባን፣ ይመሩናል ብለን ገንዘባችን ላይ እንዲያዝዙ ያስቀመጥናቸው ሰዎች እምነት አጉድለው በድህነታችን ቁስል ላይ ደረቅ እንጨት እንደከተቱበት አይተናል፡፡ ሕዝብ የገዛ ገንዘቡ ስለጠፋበት ምክንያት ከፍርድ ቤት ሒደት በፊት የማወቅ መብትም ፍላጎትም አለው፡፡ የግለሰቦች privacy ለሕዝብ ጥቅም ሲባል override ተደርጓል፡፡ ማንኛውም ጥሩ ነገር የሚገኘው በመስዋዕትነት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ በዶክመንታሪው ስማቸው የተነሱት ግለሰቦች መስዋዕትነት እንደከፈሉ የሚቆጠረው ከወንጀል ነጻ ተብለው ፍርድ ቤት በነጻ ሲያሰናብታቸው ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ ወንጀለኛ ከሆኑ override የተደረገ privacy አይኖራቸውምና፡፡

በዶክመንታሪው ስማቸው የተነሳው ግለሰቦች በፍርድ ቤት ክርክር ነጻ ቢባሉም የተዘረዘሩት ሀቆች ውሸት እንደሆኑ በሌላ ዶክመንታሪ ወይም ፕሮግራም የሚገልጹ ሌላ ሀቅ (fact) ያላቸው ሰዎች እስካልተደመጡ ድረስ ወንጀሉ አልተሰራም ሊባል አይችልም፡፡ ምንጊዜም ፍርድ ቤት በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች መቶ በመቶ ማስረጃ እስካልቀረበባቸው ድረስ (Beyond reasonable doubt) እና በክርክር ሒደቱ ተሸናፊ ካልሆኑ በነጻ ሊሰናበቱ የሚችሉበት ህጋዊ አካሄድ መኖሩ ግልጽ ነውና፡፡

ይህ ዶክመንታሪ በምን መንገድ እንደተዘጋጀ፣ ማስረጃዎች እንዴት እንደተሰበሰቡ፣ ቃለ-መጠይቅ የተደረገላቸው ሰዎች እንዴት እንደተመረጡ፣ ዶክመንታሪው ሊያሳካው የፈለገው አላማ ምን እንደሆነ የሚያውቀው በቅርበት ያዘጋጀው አካል ነው፡፡ እኔ እንደ አንድ ተመልካች ዶክመንታሪን ሳይ በይዘቱ የቀረቡ ጥሬ ሀቆችን ማመዛዘን እንጂ ከዶክመንታሪው ጀርባ ሊኖር የሚችለውን አንዳንድ ጉዳይ በማሰብ መጨነቅ አልፈልግም፡፡ ጋዜጠኝነት ከተጽዕኖ ወጦ ጠንካራ ሙያ እንዲሆን ከሚመኙ፣ ከሚፈልጉ፣ ከሚለፉ ሰዎች ውስጥ አንዱ ነኝ ብዬ ግን አስባለው፡፡ የዚህ ማስረጃ ቢያንስ ጋዜጠኝነትን አስተምራሁ፤ በማስተምራቸው ልጆቼም እኮራለሁ፡፡ ከየአቅጣጫው የሚመጣባቸውን ተጽዕኖና ውርጅብኝ ተቋቁመው የኢትዮጰያን ጋዜጠኝነት ለመታደግ ሌት ተቀን እንደሚደክሙ አውቃለሁ፡፡

ማንኛውም ዶክመንታሪ ሲዘጋጅ አላማ አለው፡፡ ያለ አላማ የሚዘጋጅ ዶክመንታሪ አይኖርም፡፡ ዶክመንታሪው የሚጫወታቸው ሚናዎችም አሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ እንደ አንድ የቴሌቪዥን ዶክመንታሪ አስተማሪ ጥቂት ሀሳብ ላካፍላችሁ፡፡ ኢሪክ ባርኖው (Erik Barnouw) የተባለው የሚዲያ ምሁር Documentary: A History of Non-Fiction Film (New York: Oxford University Press, 1974) በተሰኘው ድንቅ መጽሐፉ የዶክመንታሪ ፊልም ሚናን በተመለከተ ዝርዝር ትንታኔ ሰጧል፡፡ ባርኖው እንደሚለው የቴሌቪዥን ዶክመንታሪ ቢያንስ አስራ ሶስት ሚናዎች ሊኖሩት ይችላል፡፡ እነዚህም፡- የነብይነት (Prophet)፣ የተጓዥነት/የነቃሽነት (Explorer)፣ የዘጋቢነት (Reporter)፣ የቀራጭነት (Painter)፣ የተከራካሪነት/ጠበቃነት (Advocate), ከሳሽነት (prosecutor)፣ ጡርንባነፊነት/ ድምጽአሰሚነት (Bugler), ገጣሚነት/ ጉዳይን ከተለመደው እይታ ለየት አድርጎ የማየት ጥበብ (Poet)፣ ገድል ነጋሪነት (Chronicler)፣ ቀስቃሽነት/አስተዋዋቂነት (Promoter)፣ የንስር አይንነት (Observer)፣ ቆስቋሽነት (Catalyst)፣ ሽምቅ ተዋጊነት (Guerrilla) ናቸው፡፡ እነዚህ የዶክመንታሪ ሚናዎች እ.ኤ.አ. ከ1922 ጀምሮ በአለም ዙሪያ የተሰሩ ዶክመንታሪዎችን በመገምገም የተተነተነ ነው፡፡

ይህንን ጽሑፍ የምታነቡ ወዳጆቼ “ምናባዊው…” የተሰኘው ዶክመንታሪ ከላይ ከተጠቀሱት ሚናዎች ውስጥ የትኛውን ወይም የትኞችን ሚናዎች የተጫወተ ይመስላችኋል? ሀሳባችሁን በጨዋ ደንብ በ comment መስጫው ላይ አስፍሩ፡፡

ኢትዮጵያ በፈጣሪ ፍቃድና በልጆቿ ብርታት ታፍራና ተከብራ ትኑር!

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew