የፕሮፌሰር አስራት ደግነት፣ ትህትና እና ፈዋሽነት ጥቂት ማሳያዎች!

1) አንድ ጊዜ ከአርባ ምንጭ የመጡ አንድ ታካሚ፣ “አስራት የሚባል ፀበል ፈልቋል ስለተባልሁ ነው ወደዚህ የመጣሁት” ያሉኝን አስታውሳለሁ። ፕሮፌሰር አስራት በሽተኞችን ኦፕራሲዮን ከማድረጋቸው በፊት የመጀመሪያውን ስራ ለእግዚአብሄር ይሰጣሉ። ፀሎት ሳያደርጉ ስራቸውን አይጀምሩም።

2) 18 አመት እድሜ ያለው አንድ ግሪካዊ ኢትዮጵያ ናዝሬት ለሽርሽር መጥቶ በጥይት ይመታል። አስራት ለወጣቱ ህክምና ካደረገለት በኋላ ወደውጭ ሀገር ሄዶ ስለነበር የግሪክ ኮሚኒቲ አባላት ካገራቸው ሀኪም ለማስመጣ አፄ ኃይለስላሴን ይጠይቃሉ። ተፈቅዶላቸው ግሪካዊ ሀኪም ይመጣል። የመጣው ግሪካዊ ሀኪም አስራት ያከሙትን ግሪካዊ ወጣት መርምረው ካዩ በኋላ ለአፄ ኃይለስላሴ፣ “እኔ ከመገረምና ከመደነቅ ውጭ የምጨምረው ነገር የለም። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ አስራት ያለ ሀኪም መኖሩ አስደንቆኛል” ብሎ ነበር።

3) ሌላ ጊዜ አንዲት እንግሊዛዊት ወ/ሮ ማግደሊን ዋይን የሚባሉ ኢትዮጵያ ውስጥ እያሉ በድንገት ይታመማሉ። ህክምና ያደረጉላቸው አስራት ነበሩ። በህክምናው የተደነቁት የብሪታንያው አምባሳደር ለአስራት ደብዳቤ ሲፅፉ፣ “ተወዳጁ ሀኪም በቅድሚያ የዩኒክ ታይለር እህት በደረሰባቸው አሰቃቂ አደጋ ወቅት ላሳዩት ደግነትና ወደር ለማይገኝለት ችሎታዎ ጥልቅ ምስጋና በብርትሽ ካውንስል ስም አቀርባለሁ። ለፈፀሙት ተግባር ላቅ ያለ አድናቆት አሳድሮብኛል። ማንኛውም የሚፈልጉት ነገር ሲኖር እንዲገልፁልኝ በአክብሮት አሳውቃለሁ”። ብለዋቸዋል።
አስራት ለደብዳቤው ሲመልሱ፣ “በአሁኑ ጊዜ ገንዘብ ምንም አይደለም። ከዚህስ በላይ ለኛ ትልቁና አስፈላጊያችን ደግነትዎና ከምንም በላይ ደግሞ የችግራችን ተካፋይነትዎ ነው። ስለሆነም በድጋሜ አመሰግንዎታለሁ” የሚል ነበር።

4) አስራት ስለስራቸው አስተያየት ሲሰጣቸው፣ “ብቻዬን አይደለሁም። እግዚአብሄር እና የስራ ባልደረቦቼ አብረውኝ ናቸው” ይሉ ነበር።

(ከነፀብራቅ መጽሐፍ የተወሰደ)

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew

Leave a Reply

Your email address will not be published.