‹‹ግንብ ያስፈልጋልም አያስፈልግምም›› (መላኩ አላምረው)

‹‹ግንብ ያስፈልጋልም አያስፈልግምም›› (መላኩ አላምረው)

በአንዲት ሀገር ትንንሽ ዓሣዎች የሚረብሹት አንድ ባሕር ነበር። የዓሣዎቹ ረብሻ በሐይቁ ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎችን ሰላም አልሰጥ አለ፡፡ ትንንሾቹ ዓሣዎች በቡድን በቡድን ሆነው በመንቀሳቀስ ትልቅ ማዕበል ይፈጥሩና ውኃውን እየናጡ ወደ ሰፈር ያስገቡታል፡፡ ከዚያም የሰፈሩ ሰዎች ውኃውን ለማስወገድ ብዙ ይደክማሉ፡፡ ትንሽ ማዕበሉ ጸጥ አለ ብሎ ሰው ለመዝናናት ሲሞክር ዓሣዎቹ በድንገት ንጠው ይልኩታል፡፡ መዝናናቱ ወደ ግርግር ይለወጣል፡፡ እንዲህ እየሆነ የሰፈሩ ሰላም መመለስ አቃተው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን የሰፈሩ ሰዎች ተሰባሰቡና ማዕበሉን ስለማጥፋት መምከር ጀመሩ፡፡ ጎረምሶቹ ‹‹ለማዕበሉ ምክንያቶች ዓሣዎች ናቸው፡፡ በዋና ገብተን ዓሣዎችን ድምጥማጣቸውን ካላጠፋን አናርፍም፡፡›› ብለው ፎከሩ፡፡ ሽማግሎቹ… ‹‹ሲጀመር ማዕበሉን ለማስቆም የግድ ዓሣዎችን ማጥፋት የሚል አካሄድ ትክክል አይደለም፡፡ ሲቀጥል ዓሣዎችን በዋና እየፈለጉ ለማጥፋት መሞከር ከንቱ ድካም ነው፡፡ ሌላ መላ አምጡ›› አሏቸው፡፡
ጎረምሶቹ ትንሽ ተመካከሩና… ‹‹ከዚህ ሁሉ ነገር ለምን ባሕሩ እንዲደርቅ አናደርገውም? ባሕሩ ቢደርቅ አንድም ከማዕበሉ ረብሻ እናርፋለን፡፡ ሁለተኛም ባሕሩ የነበረበት መሬት ጥሩ ሜዳ ይሆንልናል፡፡ ለመዝናኛም ለእርሻም እንጠቀምበታለን፡፡ ስለዚህ ባሕሩን የምናደርቅበትን ስልት እንቀይስ›› አሉ፡፡ ሽማግሎቹ በጎረምሶቹ ምክርና ንግግር አዘኑ፡፡
ከሽማግሎቹ አንዱ ተነሳና እንዲህ አለ፡፡ ‹‹ልጆቼ… ይህንን በስሜት እንጅ በአእምሮ አልተናገራችሁትም፡፡ ለዚህ ሰፈር ከምንም በላይ ባሕሩ ያስፈልጋል፡፡ የማዕበሉ ሰፈራችንን የመረበሽ ችግሩ የባሕሩ መኖር አይደለም፡፡ የዓሣዎች መኖርና ቡድንተኝነትም አይደለም፡፡ ችግሩ የእኛው ነው፡፡ እኛ ማዕበሉ በዓሣም ተገፋ በሌላ… ወደ ሰፈር እንዳይገባ መከላከያ መስራት እየቻልን ዝም ብለን ተቀመጥን፡፡ የእኛ ሥራ መከላከያ መሥራት መሆን ሲገባው ማዕበሉ በተነሳ ቁጥር እርሱን ከሰፈር በማስወጣት ተጠመድን፡፡ ስለዚህ አሁን ማድረግ ያለብን ሰፈራችንን በግንብ ማጠር ነው፡፡ ማዕበሉ ዘሎት ሊያልፍ የማይችል ጠንካራ ግንብ ከገነባን ዓሣዎች ባሕሩን ሲንጡ ውለው ቢያድሩ ወደ እኛ መጥቶ አይረብሸንም፡፡ እኛን እስካልረበሸ ድረስ የባሕሩ ማዕበል ኖረ አልኖረ ምን ጨነቀን፡፡ የዓሣዎችስ መኖር ምናችንን ይነካዋል?! የሚያስነሱትን ማዕበል መመከት እስከቻልን ድረስ የዓሣዎች መኖር ይጠቅመናል እንጅ አይጎዳንም፡፡ ስለዚህ የራሳችንን የቤት ሥራ ሳንወጣ ከእኛ ውጭ በሆኑ ነገሮች መረበሽና እነርሱን ለማጥፋት መድከም ስንፍና ነው፡፡ እነርሱ በራሳቸው ተፈጥሮ ነው የሚኖሩት፡፡ እኛ ነን የእኛን መኖሪያ የመጠበቅ ኃላፊነት ያለብን፡፡ ሰላማችን በእኛ እጅ እንጅ በሌሎች መኖር አለመኖር የሚወሰን አይደለም፡፡ በሉ ተነሱና ግንብ እንገንባ፡፡ ማዕበል የማያናውጠው ጠንካራ ግንብ፡፡››
ሁሉም በሽማግሌው ሐሳብ ተስማሙ፡፡ ግንቡም ተገነባ፡፡ ማዕበሉም ወደ ሰፈር መግባት አቆመ፡፡ ሰላምና ጸጥታ ሆነ፡፡

ጀርመን ለሁለት በተከፈለች ጊዜ በመሐል ትልቅ ግንብ ገነቡ፡፡ ዳግም ላለመገናኘት ወስነው በግንብ ተለያዩ፡፡ ተለያይተው ግን ዝም አላሉም፡፡ ምሥራቆቹ ወደ ምዕራቦች ሁሌም ጭቃ በግንቡ እያሳለፉ ይወረዉሩላቸው ነበር፡፡ ምዕራቦቹ ግን መልሰው ጭቃ አይወረውሩም፡፡ ይልቁንስ ክሬም ያለው ኬክ ይወረውሩላቸው ነበር እንጅ፡፡ በዚህ መልኩ ዓመታት አለፉ፡፡ ከዚያም ምሥራቆች መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ‹‹እንዴት ይህን ያህል ዘመን እኛ ጭቃ እየወረወርን እነርሱ ኬክ ይመልሱልናል?›› አሉ፡፡ ከዚያም ደብዳቤ ጻፉና ወረወሩላቸው፡፡ ‹‹እንዴት ይህን ያህል ዘመን እኛ ጭቃ እየወረወርን እናንተ ግን ኬክ ትመልሱልናላችሁ? እባካችሁ በጥፋታችን ይቅር በሉን…›› የሚል፡፡ ምዕራቦቹም መለሱ፡፡ ‹‹እናንተ ባደረጋችሁት አንድም ቀን ተቀይመን አናውቅም፡፡ ምክንያቱም ሰው የሚወረውረው ያለውን ነውና፡፡ ከጭቃ የተሻለ ነገር ቢኖራችሁ ያንን እንደምትወረውሩልን እናምናለን፡፡ እናም እናንተ የሌላችሁን ከየት አምጥታችሁ ትወረውሩልን ዘንድ ፈልገን እንቀየማለን? ይልቅ እንታረቅ›› ብለው ጻፉ፡፡ በዚህ መልኩ መግባባት ጀመሩ፡፡ ታረቁም፡፡ ግንቡም ፈረሰ፡፡

አንደኛ፡-

ማዕበል በተነሳ ቁጥር የማዕበሉን አስነሽ/በጥባጮችን ለማጥፋ ከመሮጥ ይልቅ ማዕበል የማያናውጠው ግንብ እንገንባ፡፡ ጥላቻ የማይሻገረው የፍቅር ግንብ፡፡ በቀል የማያናውጠው የይቅርታ ግንብ፡፡ ከፋፋዮች የማይሻገሩት የአንድነት ግንብ፡፡ ተንኮለኞች በሴራና በወሬ የማያጠፉት የመተማመኛ ግንብ፡፡
ሁሌም በራሳችን ጠንክሮ መቆም እንጅ በሌሎች መኖር/አለመኖር አንጨነቅም/አንተማመንም፡፡ ሕልውናችንን የማስቀጠል መብቱም ግዴታውም የእኛ ነው፡፡ ሌሎች ሊያጠፉን የሚችሉት የሚጠፋ ቁመና ካለን ብቻ ነው፡፡ ከእነርሱ የማጥፋት አቅም በተሻለ የመኖር ከፍታ ላይ ከቆምን የእነርሱ መኖር አለመኖር ሊያሳስበን አይችልም፡፡

ሁለተኛ፡-

አንድነትን ካሰብን ለድንጋይ ድንጋይ መመለስ አይገባም፡፡ እኛ ከድንጋይ የተሻለ ነገር መወርወር አለብን፡፡ ከድንጋይ የተሻለ ነገር ለመወርወር ግን ከድንጋይ የተሻለ ሀብት ሊኖረን ይገባል፡፡ ልቡ በቀልን ብቻ የሚያከማች አንደበቱ የፍቅርና ይቅርታና ቃል ከየት አምጥቶ ይተፋል? ልቡ በፍቅር የተመላ ሰውስ ለሰድብ ስድብን ለምን ይመልሳል? ካለው የፍቅር መዝገብ የይቅርታን ቃል ይወርውር እንጅ፡፡ ሁሉም ኖሮት ከተረፈው ይሰጣልና፡፡ የመከፋፈል ግንብ ሊፈርስ የሚችለው በአቻ ውርዋሮሽ አይደለም፡፡ ከጠመመው ጋር አብሮ በመጥመም የሚቃጠጥ ነገር የለም፡፡ ተሽሎ የማይገኝ የተሻለ ነገን መፍጠር አይችልም፡፡ ከቂምና ከበቀል ያልጸዳ ሌላውን የመውቀስ ሕሊና አይኖረውም፡፡ ከፋፋይ ግንቦች የሚፈርሱት በፍቅርና ይቅርታ ብቻ ነው፡፡ ይቅር የሚባል ደግሞ የበደለ ነው፡፡ ንሰሐ የሚያስፈልገው ኃጢአተኛ ነውና፡፡ ችግሩ…. ‹‹ለበደልሁት ይቅርታ አልጠይቅም፡፡ በቀሌንም አላቆምም›› ካለ ነው፡፡ ለዚህ መልስ የለኝም፡፡ ተፈጥሮ ግን ሚዛናዊ ፍርጃ አላትና…. ለሁሉም የዘራውን ታሳጭደዋለች፡፡ የተፈጥሮ ፈጣሪ ያዳላ ዘንድ ሰው አይደለም፡፡

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew