ፓትርያርክና ፕትርክና / ዲ/ን ዳንኤል ክብረት

ከሰባት ዓመታት በፊት ነበር፤ ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቃለ መጠይቅ ማድረግ በመንበረ ፓትርያርክ ግቢ በሚገኘው ቢሯቸው ወደ አሥር ሰዓት አካባቢ ከሌሎች ባልደረቦቼ ጋር ተገኝቼ ነበር፡፡ ያ ቃለ መጠይቅ ወደ አራት ሰዓታት ያህል የፈጀና በሐመር መጽሔት ላይ በተከታታይ የወጣ ነበር፡፡

በመካከል ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱ በወቅቱ የነበረችበትን ሁኔታ የሚያነሣ አንድ ጥያቄ ተሰነዘረላቸው፡፡ መጀመርያ በመዳፋቸው አገጫቸውን ያዙና ወደ ጠረጲዛቸው አንገታቸውን ደፉ፡፡ በዚያም ለረጅም ሰዓት አቀርቅረው ቆዩ፡፡ ምን እያሰቡ ይሆን ብለን እናስብ ነበር፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ቀና ሲሉ ዕንባዎቻቸው በሁለቱም ጉንጮቻቸው ላይ መንታ ሆነው ይፈሱ ነበር፡፡ ምንም አላሉንም፡፡ ዝም ብለው አዩን፡፡ ከዚያም ይቀረጹበት የነበረውን ቪዲዮ እንዲጠፋ አዘዙ፡፡ እኛንም ተቀመጡ አሉን፡፡ ግራ ገብቶን ተቀመጥን፡፡

ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ያን ዕለት ሲናገሩት የነበረውን ነገር ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ሲናገሩት ሰምቼ አላውቅም፡፡ ሲነግሩን ያለቅሱ ነበር፡፡ እኛም ብንሆን በኀዘን ድባብ ውስጥ ነበርን፡፡

ከዚያች ቀን ጀምሮ ስለ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ያለኝ አመለካከት የተዘበራረቀ ሆነ፡፡ የሚወስዷቸውን ርምጃዎች፣ የሚያሳዩዋቸውን ጠባያት፣ የሚፈጽሟቸውን ተግባራት ስመለከት ምን ዓይነት ሰው ናቸው? ያሰኘኛል፡፡ የዚያን ቀን ሁኔታቸውን ሳስበው ደግሞ እኒህ አባት ሁላችንም ያላወቅንላቸው የተደበቀ መልካም ሰብእና ይኖራቸው ይሆን? እላለሁ፡፡ ያ ዕንባ ዝም ብሎ የመጣ የተዋናይ ዕንባ እንዳልነበረ እኔ ራሴ በዓይኔ ያሁት ነው፡፡ በዚያች ሰዓት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን እየደረሰባት ስላለው ፈተና የነገሩን ነገር በኋላ ይወስዷቸው ከነበሩት ርምጃዎች ጋር አልጣጣም እያሉኝ እቸገር ነበር፡፡

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አምስተኛ ፓትርያርክ ናቸው፡፡ ከአቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን እስከ መጨረሻው ግብጻዊ ጳጳስ እስከ አቡነ ቄርሎስ ድረስ አንድ መቶ አሥራ አንድ ጳጳሳት ከግብፅ መጥተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የፓትርያርክ ሹመት ከፖለቲካ ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ የአቡነ ባስልዮስን የአቡነ ቴዎፍሎስ ሹመት ከዐፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር፣ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትና የአቡነ መርቆሬዎስም ሹመት ከደርግ ጋር፣ የአቡነ ጳውሎስም ሹመት ከኢሕአዴግ ጋር እየተያዘ ይነሣል፡፡ ቤተ ክህነቱንም አንድ ጊዜ ሸዋ አንድ ጊዜ ጎጃም፣ አንድ ጊዜ ጎንደር፣ አንድ ጊዜ ትግራይ ባለቤት ሲመስልበት ከዘረኛነት ወቀሳ ነጻ ሳይሆን እኛ ዘመን ደርሷል፡፡

ባስልዮስ ወቴዎፍሎስ ሊቃነ መላእክት እሙንቱ

ለሙሴ ቤተ ክህነት ቀበርዎ በሕይወቱ

የሚለው ቀኔ ቀድሞም ጀምሮ አባቶችን በአስተዳደራቸው የተነሣ መውቀስ የቤተ ክህነቱ ገንዘቡ እንደነበረ ያሳየናል፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለፓትርያርክነት ሹመት አዲስ በመሆንዋ የዳበረ ልምድና አሠራር የላትም፡፡ የመጀመርያው ፓትርያርክ አቡነ ባስልዮስ እጨጌ ስለ ነበሩ በዚያው ነው ወደ ፕትርክናው የሄዱት፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስም ከእንደራሴነት ወደ ፕትርክና ሲሻገሩ ያንን ያህል የምርጫና የአሠራር ሕግ አላስፈለገም፡፡ የእርሳቸው ሞት ሳይታወጅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሲሾሙም ቤተ ክርስቲያኒቱ በቀደምቱ ሁለት ፓትርያርኮች ምርጫ ያልተከተለችውን አዲስ አሠራር አምጥታ ከመነኮሳት መካከል ነው የመረጠችው፡፡ አቡነ መርቆሬዎስና የአቡነ ጳውሎስ አመራረጥም አወዛጋቢና የሌሎች እጅ የነበረበት ነበር፡፡

ይህ ዓይነቱ ችግር በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ውስጥ የተከሰተና አያሌ ፈተናዎችንም ያመጣ ነው፡፡

በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፓትርያርኮች በተለያዩ መንገድ ወደ መንበረ ማርቆስ መጥተዋል፡፡ በአንዳንድ ታሪኮች ነባሩ ፓትርያርክ ከእርሱ በኋላ በመንበሩ የሚቀመጠውን የሰየመበት ታሪክ አለ፡፡ ሁለተኛውን የእስክንድርያ ፓትርያርክ አንያኖስን የመረጠው የመጀመርያው ፓትርያርክ ቅዱስ ማርቆስ ነበር፡፡ በዘመን መለወጫ ዕለት አዘውትረን ስሙን የምንጠራው አባት ድሜጥሮስ ለመንበረ ማርቆስ የተመረጠው ከእርሱ በፊት በነበረው ልያኖስ በተባለው አባት ነበር፡፡ ታላቁን ሐዋርያዊ አባት አትናቴዎስንም ወደ መንበር ያመጣው እለ እስክንድሮስ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ምእመናኑና አባቶች በአንድነት የተስማሙበትን አባት በመንበረ ማርቆስ ያስቀ መጡበትም ጊዜ ነበር፡፡ በመሠዊያው ላይ ከጸሎት በኋላ በሚደረግ የዕጣ ሥነ ሥርዓት ፓትርያርኩ የተመረጡበት ጊዜም አለ፡፡ ብጹዕ አቡነ ሺኖዳ የተመረጡት አስቀድሞ ብዙ ድምጽ ካገኙ ሦስት አባቶች መካከል በተደረገ ዕጣ ነበር፡፡

በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደምናየው በፓትርያርኮች ምርጫ እና አገልግሎት ላይ በወቅቱ የነበሩ መሪዎች ጫና ያደረጉበት፤ ከዚያም አልፈው የራሳቸውን ሰው የሾሙበትም ጊዜ ነበር፡፡ ለምሳሌ ሐዋርያዊው አትናቴዎስ በግፍ ከመንበሩ ተሰድዶ በነበረ ጊዜ ባዛንታናውያን የራሳቸውን ፓትርያርክ መርጠው ጎርጎርዮስ ብለው ልከውት ነበር፡፡ እርሱም በመንበረ ማርቆስ ላይ ከ339–346 ዓም ተቀምጦ ነበር፡፡ የእስክንድርያ ክርስቲያኖች ግን አልተቀ በሉትም፡፡ በዚህም ምክንያት ከፓትርያርኮች ዝርዝር አያስገቡትም፡፡

በተለይም በኬልቄዶን ጉባኤ ዲዮስቆሮስ መከራ ከደረሰበት በኋላ መንበረ ማርቆስ የባዛንታይን መንግሥት በሚልካቸው ፓትርያርኮችና የእስክንድርያ ቅዱስ ሲኖዶስ በመረጣቸው አባቶች ሲፈራረቅ ነበር፡፡ በመንበሩ የተቀመጠውን ኦርቶዶክሳዊ ቀኖናዊ አባት በወታደር ኃይል እያሳደዱ የራሳቸውን ሰው መመደብን የባዛንታይን ነገሥታት ለመቶ ዓመታት ያህል ቀጥለውበት ነበር፡፡ ሕዝቡ ግን አልተቀበላቸውም፤ ከቁጥርም አያስገባቸውም፡፡

በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ የዑምያድ ሥርወ መንግሥት አክትሞ የአባሲድ ሥርወ መንግሥት ሲተካ በግብጽ፣ በሶርያ እና በአካባቢው አለመረጋጋት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ለመሾም ከባድ ሆኖ ነበር፡፡ አስቀድመው የነበሩት ፓትርያርክ ዐርፈው በመንበሩ ያለ በዐለ መንበር ተቀመጦ ነበር፡፡

ሁኔታውን የተመለከተውና በወቅቱ ከነበረው የሶርያ ገዥ ጋር ቅርበት የነበረው በአንጾኪያ የካራን ሀገረ ስብከት ጳጳስ የነበረው አቡነ ይስሐቅ መንበሩን መረከብ ፈለገ፡፡ ለዚህ ሃሳቡም የካራንን አባሲድ ገዥ ከሊፋ አብዱላህ አቡ ጋፋርን ከጎኑ አሰለፈ፡፡ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ‹‹የአባቶቻችን ቀኖና ሀገረ ስብከት ያለው ጳጳስ ፓትርያርክ እንዳይሆን ይከለክላል፤ በሌላም በኩል ማንም አባት ክህነትንም ሆነ ሥልጣንን ለማግኘት ብሎ የዓለማዊ መንግሥታትን የተማጸነ ይወገዝ ብለው አባቶቻችን ቀኖና ሠርተዋልና አንቀበልህም›› አሉት፡፡

ከሊፋ አብዱላህ አቡ ጋፋር በሲኖዶሱ ውሳኔ ተበሳጭቶ ሁለት ጳጳሳትን አስገደላቸው፡፡ አቡነ ይስሐቅንም በኃይል በመንበረ ዮሐንስ ላይ አስቀመጠው፡፡ አቡነ ይስሐቅም የእርሱን ፓትርያርክነት የእስክንድርያው ፓትርያርክ አቡነ ሚካኤል አንደኛ (744-767) ያውቅለት ዘንድ ደብዳቤና ስጦታ ወደ እስክንድርያ ላከ፡፡

አቡነ ሚካኤል የአቡነ ይስሐቅን ደብዳቤ ከተመለከተ በኋላ ከቤተ ክርስቲያን ቀኖና ውጭ ሕግን በመጣስና ያለ ቅዱስ ሲኖዶሱ ፈቃድ የተሾመ በመሆኑ እንደማይቀበለው ለመልክተኞቹ ገለጠላቸው፡፡ መልክተኞቹም ጉዳዩን ወደ ግብጹ ገዥ አቀረቡት፡፡ የግብጹ ገዥ ከከሊፋ አብዱላህ ጋር መጋጨት ስላልፈለገ አቡነ ሚካኤል የአቡነ ይስሐቅን ሹመት እንዲቀበሉት አዘዘ፡፡
አቡነ ሚካኤልም ሲኖዶሱን ለመሰብሰብ የሦስት ቀን ጊዜ ጠየቁ፡፡ ነገር ግን የእስክንድርያ ሲኖዶስ ከቤተ ክርስቲያን ቀኖናና ታሪክ አንጻር ጉዳዩን በማየት አንድ ወር ወሰደ፡፡ በዚህ ጊዜም

1. ሀገረ ስብከት ያለው አባት ሀገረ ስብከቱን መተው ወደ ሌላ ሹመትም መሄድ እንደሌለበት ቀደምት አበው መወሰናቸውን

2. በዓለማዊ ባለ ሥልጣን ድጋፍ ወደ መንበር የሚመጣ ጳጳስ ቢኖር ከሹመቱ እንዲሻር የቤተ ክርስቲያን ቀኖና እንደሚያዝ

በመጨረሻም ዛሬ የአቡነ ሚካኤል ቀኖና የሚባለውን ውሳኔ በመወሰን የአቡነ ይስሐቅን ሹመት እንደማይቀበለው ገለጠ፡፡ መልክተኞቹም ለግብጹ ገዥ ጉዳዩን አቀረቡ፡፡ የግብጹ ገዥ በልመና ጭምር ለማግባባት ሞከረ፡፡ ግን አልሆነም፡፡ በመጨረሻም መልክተኞቹ አቡነ ሚካኤልን ከእነርሱ ጋር ከሊፋ አብዱላህ ወዳለበት ወደ ካራን እንዲሰድደው ጠየቁት፡፡
አቡነ ሚካኤል ወደ ካራን ሄዶ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና የሚደርስበትን ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ገለጸ፡፡ ሁለት ጳጳሳትም አብረውት ለመሄድ ተነሡ፡፡ መልክተኞቹና አቡነ ሚካኤል ወደ ካራን ለማምራት በዝግጅት ላይ እያሉ አቡነ ይስሐቅ በሕዝቡ ጸሎት ምክንያት ማረፉ ከአንጾኪያ ተሰማ፡፡ ነገሩም በዚሁ አበቃ፡፡

የግብጽ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ በተፈጠሩ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች ለዓመታት በዐቃቤ መንበር የተመራበት ዘመን ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ይፈጠር የነበረው በአንድ በኩል ነባሮቹ ፓትርያርኮች በገዥዎች ተግዘው ወይም ታሥረው መንበሩ ባዶ ሲሆን፤ ያለበለዚያም ደግሞ ነባሮቹ ፓትርያርኮች ዐርፈው በቀጣዩ አባት ምርጫ ላይ በምእመናኑና በአባቶች፣ በአባቶችና በአባቶች፣ እንደዚሁም በቤተ ክርስቲያኒቱና በገዥዎቹ መካከል ስምምነት ሲጠፋ ነው፡፡

ከአቡነ ዮሐንስ 19ኛ (1928–1942) በኋላ ለሁለት ዓመት፤ ከአቡነ መቃርዮስ 3ኛ (1944–1945) በኋላ ለአንድ ዓመት፤ ከአቡነ ዮሐንስ 2ኛ (1946–1956) በኋላ ዓመታት መንበረ ማርቆስ በዐቃቤ መንበር ብቻ ለመመራት ተገድዶ ነበር፡፡

አቡነ ሺኖዳ 3ኛ በመንበረ ማርቆስ ላይ ከተቀመጡ ከዐሥር ዓመት በኋላ ከአንዋር ሳዳት ጋር ስምምነት አልነበራቸውም፡፡ በተለይም ደግሞ በግብጽ አብያተ ክርስቲያናትና ምእመናን ላይ የሚደርሰውን ግፍ ለማስቆም መንግሥት ዝም በማለቱ አርሳቸው ፊት ለፊት የሳዳትን መንግሥት መተቸት ጀመሩ፡፡ ይህም አንዋር ሳዳትን ስላበሳጨው የግብጽ ሚዲያዎች በይፋ ፓትርያርኩን የሚያቃልሉ ፕሮግራሞችን ማቅረብ ጀመሩ፡፡ በመጨረሻም አንዋር ሳዳት አቡነ ሺኖዳን በ1981 ዓም ከመንበራቸው አንሥቶ በግዞት ወደ አባ ብሶይ ገዳም ላካቸው፡፡

የግብጽ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ሁኔታውን በተመለከተ በሁለት ሃሳብ ተከፈለ፡፡ በአቡነ ሳሙኤል የሚመራው አካል ሺኖዳን በኃይለኛነት በመውቀስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከመንግሥት ጋር እንድትጋጭ በማድረግ ችግር ውስጥ ከትተዋታል ብሎ አቋም ያዘ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ‹‹ለቤተ ክርስቲያናቸው ሲሉ የወሰዱት ትክክለኛ አቋም ነው›› ብለው አወደሷቸው፡፡ ከእርሳቸውም ጋር አብረው ተሰደዱ፡፡ ምንም እንኳን ሳዳት አቡነ ሺኖዳን ‹‹የቀድሞው ፓትርያርክ›› ቢላቸውም አብዛኞቹ ጳጳሳትና ምእመናን ይህንን አልተቀበሉትም ነበር፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱ ሲኖዶስም በአቡነ ሺኖዳ ምትክ ሌላ አባት መሰየሙን አልተቀበለውም፡፡ በምትኩ የጳጳሳት ኮሚቴ ተቋቁሞ ቤተ ክርስቲያኒቱን መምራት ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ እጅግ የታወቁት የገዳማት አባቶች ሳይቀሩ የአቡነ ሺኖዳን ሃሳብ የተቃወሙበት ጊዜ ነበር፡፡ ታዋቂው የአባ መቃርዮስ ገዳም አበ ምኔት መታ አል ምስኪን አቡነ ሺኖዳ የተሾሙበትን ጊዜ ‹‹ የቤተ ክርስቲያን የመከራ ዘመን መጀመርያ›› እስከ ማለት ደርሰው ነበር፡፡

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የመካከለኛው ዘመን ታሪክም ‹‹የሦስት ፖፖች ታሪክ›› የሚባል ምዕራፍ አለ፡፡ ይህ ምዕራፍ በሮም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከ1378 እስከ 1417 ዓም ድረስ በአንድ ወቅት ሁለት ፖፖች ራሳቸውን ሕጋዊ ፖፕ አድርገው ያቀረቡበት ጊዜ ነው፡፡ የሮም ቤተ ክርስቲያን መንበር ወደ ሮም ከተመለሰ በኋላ ፈረንሳይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ታደርግ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩት ፖፕ ጎርጎርዮስ 11ኛ ሲያርፉ የሮም ሲኖዶስ የፈረንሳይን መንግሥት ተጽዕን በመፍራት ምንም ዓይነት ሮማዊ ዕጩ ሳይቀርብ ናፖሊታናዊውን ኡርባን 6ኛን በ1378 ሾሙ፡፡ ነገር ግን ከጥቂት ቀናት በኋላ የፖፕ ኡርባን ጠባይና አሠራር ተበላሸ፡፡ ሿሚዎቹም መፀፀት ጀመሩ፡፡ ብዙዎቹም በመካከለኛው ጣልያን ከሮም ምሥራቅ ደቡብ ምሥራቅ ወደ ምትገኘው አናኒ ከተማ ራሳቸውን አሸሹ፡፡

በአናኒ ከተማ የተሰበሰቡት የካቶሊክ ካርዲናሎችም ፖፕ ኡርባን በመንበራቸው ላይ እያሉ የጄኔቫውን ሮበርት ፖፕ ቀሌምንጦስ 7ኛ ብለው በዚያው ዓመት መስከረም 9 ቀን ሾሙ፡፡ ይህም የብጥብጡ መነሻ ሆነ፡፡ ዮፖፑንም መቀመጫ ወደ በአቪግኖን አደረጉት፡፡ ፈረንሳይ፣ አራጎን፣ ቆጵሮስ፣ ቡርጉንዲ፣ ሳቮይ፣ ኔፕልስ፣ እና ስኮትላንድ የአቪግኖን ፖፕ ተቀበሉ፡፡ ዴንማርክ፣ እንግሊዝ፣ ፍላደርስ፣ የሮም መንግሥት፣ ሐንጋሪ፣ አየርላንድ፣ ኖርዌይ፣ ፖላንድ፣ ስዊዲንና የቬነስ ሪፐብሊክ ደግሞ ሮም ላይ የተቀመጠውን ፖፕ ደገፉ፡፡

ይህ የመንበርና የሕጋዊነት ጥያቄ ሁለቱም ፖፖች ካለፉም በኋላ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች እየተሰጠው ቀጠለ፡፡ ችግሩን ለመፍታት ለብዙ ዘመናት የተደረገው የዲፕሎማሲም ሆነ የኃይል ጥረት ውጤት አላመጣም፡፡ ሁለቱ ፖፖችን ይደግፉ የነበሩት ካርዲናሎች በ1409 ዓም ፒሳ በተባለች ከተማ ተሰብስበው ሁለቱንም ፖፖች በመተው ሌላ ፖፕ ለመምረጥ ተስማሙ፡፡ በዚህም መሠረት አሌክሳንደር 5ኛ የተባሉትን ፖፕ መረጡ፡፡ ነገር ግን በሊቃውንቱም ሆነ በምእመናኑ ዘንድ ድጋፍ አላገኘም፡፡ ከፖፕ አሌክሳንደር ቀጥሎም ተቃዋሚው ፖፕ ዮሐንስ 23ኛ (anti pope) በዚሁ መንገድ ተመረጡ፡፡ ጭቅጭቁ ግን ቀጠለ፡፡

አን ግሪሰን የተባሉ ሊቅ ባደረጉት ጥረት ቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶችና ምእመናን በመተባበር በ1414 ዓም የኮንስታንስ ጉባኤ የሚባለውን ጠሩ፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ ሦስተኛው ፖፕ አቡነ ዮሐንስ 23ኛ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለመተው ተስማሙ፡፡ በሮም የነበሩት ፖፕ ጎርጎርዮስ 12ኛም ለቤተ ክርስቲያኒቱ ደኅንነት ሲሉ መንበራቸውን ለመተው ተስማሙ፡፡ ጉባኤው ይህንን ካገኘ በኋላ በአቪግኖን የነበሩትን ፖፕ ቤነዲክት 13ኛን ተመሳሳይ ተግባር ያከናውኑ ዘንድ ጠየቀ፡፡ እርሳቸው ግን ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

በዚህም የተነሣ ጉባኤው ፖፕ ቤነዲክት 13ኛን አወገዘ፡፡ በዚያው ጉባኤም ችግሩን ዘግቶ ከሦስቱም ውጭ የሆኑትን ፖፕ ማርቲን 5ኛን መረጠ፡፡ ነገር ግን የአቪግኖን ካርዲናሎችና አንዳንድ ወገኖች አዲሱን ፖፕ በመቃወም አቡነ ቤነዲክትን መደገፋቸውን ቀጠሉ፡፡ ከአቡነ ቤነዲክት 13ኛ በኋላም ሦስት ተከታታይ ፖፖችን መረጡ፡፡ በመጨረሻ ግን በአቪግኖን መንበር የተሾሙት አቡነ ቀሌምንጦስ 8ኛ ለቤተ ክርስቲያኒቱ በማሰብ በፈቃዳቸው ሹመታቸውን በመተው በ1429 ዓም በሮም ለተሰየሙት አቡነ ማርቲን 5ኛ ድጋፋቸውን ሰጡ፡፡
በግብጽም ሆነ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስናይ በፓትርያርክ ምርጫ ጊዜ የሚፈጠሩት ችግሮች ከአራት ምክንያቶች የሚመነጩ ነበሩ፡፡ የመጀመርያው ቤተ ክርስቲያኒቱ በሌሎች ተጽዕኖ ሥር ስትወድቅ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች በሚፈጠሩ ክርክሮች የተነሣ ነው፡፡ ሦስተኛው ምክንያት አባቶች የሓሳብ አንድነት በሚያጡበት ጊዜ ሲሆን አራተኛው ደግሞ ሀገራዊ ጉዳዮች አስገዳጅ ሲሆኑ ነው፡፡

Facebook Comments

Post Author: መላኩ አላምረው

መላኩ አላምረው
Melaku Alamrew